ትንቢተ አሞጽ 8
8
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነበረ። 2እርሱም፦ አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ፦ ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም። 3የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።
4ችጋረኛውን የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ፦ 5እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥ 6ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ። 7እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ ሥራቸውን ሁሉ ለዘላለም ምንም አልረሳም። 8በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሙላዋም እንደ ወንዙ ትነሣለች፥ እንደ ግብጽም ወንዝ ትነሣለች ደግሞም ትወርዳለች። 9በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለሁ። 10ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፥ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ራስ መንጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፥ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ።
11እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። 12ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፥ አያገኙትምም። 13በዚያ ቀን መልካካሞች ደናግል ጐበዛዝትም በጥም ይዝላሉ። 14በሰማርያ ኃጢአት የሚምሉና፦ ዳን ሆይ፥ ሕያው አምላክህን! ደግሞ፦ ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ! ብለው የሚሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ደግሞም አይነሡም።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 8: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in