አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 4
4
1እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጉ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፥ ፍልስጥኤማውያንም በአፌቅ ሰፈሩ። 2ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፥ ሰልፋም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፥ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ። 3ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች፦ ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄድ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ። 4ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።
5የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች። 6ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፦ በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ። 7ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው፥ እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ፦ ወዮልን፥ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም። 8ወዮልን፥ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። 9እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፥ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ። 10ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፥ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፥ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። 11የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።
12በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ። 13በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፥ ሰውዮውም ወደ ከተማይቱ ገብቶ ባወራ ጊዜ ከተማይቱ ሁሉ ተጭዋጭዋኽች። 14ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ በሰማ ጊዜ፥ ይህ ጫጫታ ምንድር ነው? አለ። ሰውዮውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው። 15ዔሊም የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበረ፥ ዓይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር። 16ሰውዮውም ዔሊን፦ ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው። 17ወሬኛውም መልሶ፦ እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፥ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ። 18ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፥ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት ፈራጅ ነበረ።
19ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፥ የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች። 20ወደ ሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች፦ ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም። 21እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለ አማትዋና ስለ ባልዋም፦ ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም፦ ኢካቦድ ብላ ጠራችው። 22እርስዋም፦ የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 4: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in