YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3

3
1ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፥ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፥ ራእይም አይገለጥም ነበር። 2በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፥ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር። 3ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔርም መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥ 4እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፥ እርሱም፦ እነሆኝ አለ። 5ወደ ዔሊም ሮጠ፦ እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም፦ አልጠራሁህም፥ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ። 6እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፦ እነሆኝ የጠራኸኝ አለ። 7እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፥ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ። ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበረ፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር። 8እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፦ እነሆኝ የጠራኽኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ። 9ዔሊም ሳሙኤልን፦ ሄደህ ተኛ፥ ቢጠራህም፦ አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ። 10እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም፦ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፦ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለ። 11እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፦ እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ። 12በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፥ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ። 13ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤቱ ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ። 14ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።
15ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ። 16ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ፦ ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፥ እርሱም፦ እነሆኝ አለ። 17እርሱም፦ እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፥ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኽኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው። 18ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም፦ እርሱ እግዚአብሔር ነው፥ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
19ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር። 20እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ። 21እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፥ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in