መጽሐፈ ምሳሌ 2
2
ከጥበብ የሚገኝ በረከት
1ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥
ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥
2ጆሮህ ጥበብን ትሰማለች፥
ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ።
ልብህንም ልጅህን ለመምከር ታቀርባለህ፥
3ጥበብን ብትጠራት፥ ቃልህንም ለማስተዋል ብትሰጥ፥
ዕውቀትንም በታላቅ ቃል ብትፈልጋት፥
4እርስዋንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥
እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤
5የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥
አምላክን ማወቅንም ታገኛለህ።
6እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤
ከፊቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤
7እርሱ ቅንነትን ለሚያደርጉ ደኅንነትን ያከማቻል፤
በመንገዳቸውም ይቆምላቸዋል።
8የጽድቅን ጎዳና ይጠብቃል፤
የሚፈሩትንም መንገድ ያጸናል።
9የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ታውቃለህ፤
መልካም መንገድንም ሁሉ ታቃናለህ።
10ጥበብ ወደ ልብህ በመጣች ጊዜ፥
ዕውቀትም ለነፍስህ መልካምና ክብር በሆነች ጊዜ፥
11መልካም ምክር ትጠብቅሃለች፤
የተቀደሰች ማስተዋልም ትጋርድሃለች።
12አንተን ከክፉ መንገድ፥
ምንም የሚታመን ነገርን ከማይናገር ሰውም ታድንህ ዘንድ፥
13እነርሱ በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ
የቀናውን ጎዳና ለሚተዉ፥
14ክፉ በመሥራት ደስ ለሚላቸው
ክፋትንም በመመለስ ሐሤትን ለሚያደርጉ፥
15መንገዳቸው ጐጻጕጽ፥
አካሄዳቸው ጠማማ ለሆኑ ወዮላቸው!
16ከቀናች መንገድ እንዳያርቁህ፥
እውነትንም ከማወቅ የተለየህ እንዳያደርጉህ፤
ልጄ ሆይ፥ በሕፃንነትህ ትምህርትን የምታስተው፥
ክፉ ምክር አታግኝህ፤
17ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ፥
ቃሏን ከምታለዝብ ከሌላዪቱ ክፉ ሴት፥
የሕፃንንነት ባልዋን ከምትተው፥
የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከምትረሳ፤ ይጠብቅህ ዘንድ፤#ምዕ. 2 ቍ. 17 በግሪኩ የተለየ ነው።
18ቤቷን በሞት አጠገብ አኖረች፥
አካሄድዋንም ከኀያላን ጋር ከምድር ወደ ሲኦል አቀናች።
19ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥
ቀና መንገዶችንም አያገኙም፥
ሕይወት በአለው ዘመንም አይገኙም።
20ቀና መንገዶችን ቢሄዱ
ለስላሳ የጽድቅ መንገዶችን ባገኙ ነበር።
21ደጋግ ሰዎች በምድር ላይ ይቀመጣሉ፥
ጻድቃንም በእርስዋ ይኖራሉ፤
22የክፉዎች መንገዶች ከምድር ላይ ይጠፋሉ፤
ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይሰደዳሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 2: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in