YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 1

1
1ለእስራኤል የነገሠ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤
2ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥
የጥበብንም ቃል ለማወቅ፥
3የቃልን መልስ ለመቀበል
በእውነት ጽድቅንም ለማወቅ
ፍርድንም ለማቃናት፥
4ብልሃትን ለየውሃን ይሰጥ ዘንድ
ለሕፃናትና ለወጣቶችም አእምሮንና ዕውቀትን፥
5ጠቢብ እነዚህን በመስማት ጥበብን ይጨምራል፥
አስተዋይ ግን ምክርን ገንዘብ ያደርጋል።
6ምሳሌንና የተሸሸገውን ነገር፥
የጠቢባንን ቃልና ዕንቈቅልሾችን ያውቃል።
ምክር ለወጣቶች
7የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤
ዕውቀት ለሚያደርጋት ሁሉ መልካም ናት።
እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፥
ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
8ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥
የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤
9ለራስህ የክብር ዘውድን
ለአንገትህም የወርቅ ድሪ ታገኛለህና።
10ልጄ ሆይ፥ ዝንጉዎች ሰዎች አያስቱህ፤
እሽም አትበላቸው።
11“ና ከእኛ ጋር ደምን በማፍሰስ አንድ ሁን፥
ጻድቅ ሰውንም በምድር እንቅበር፥ ብለው ቢማልዱህ፥
12በሕይወት ሳለ እንደ ሲኦል እንዋጠው፥
መታሰቢያውንም ከምድር እናጥፋ፤
13ብዙ ሀብቱን እንሰብስብ፥
ከምርኮውም ቤታችንን እንሙላ፤
14ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤
ለሁላችንም አንድ ከረጢትና አንድ አቁማዳ ይሁንልን” ቢሉ፥
15ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥
ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤
16እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥
ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና።
17ወጥመድን ለወፎች በከንቱ የሚያጠምዱ አይደለምና፥
18መግደልን የለመዱ እነርሱ ክፋትን ለራሳቸው ይሰበስባሉ።
የኀጢአተኞች ሰዎች አወዳደቃቸው ክፉ ነው።
19ይህ መንገድ ኀጢአትን የሚፈጽሙ ሁሉ ነው።
ቅሚያ ነፍሳቸውን ታጠፋለች።
የጥበብ ጥሪ
20ጥበብ በጎዳና ትመሰገናለች፤
በአደባባይም ድምፅዋን ትሰጣለች።
21በግንብ ድምድማት ትሰብካለች፥
በኀያላን በሮች ታገለግላለች።
በከተማ በሮች በድፍረት እንዲህ ትላለች፦
22“ይህን ያህል ዘመን የዋሃን ጽድቅን ሲከተሉ አያፍሩም።
ሰነፎች፥ እስከ መቼ ድረስ ስሕተትን ትወዳላችሁ?
ሰነፎች ስድብን የሚወዱ ናቸው፥
ሰነፎችም ሆነው ዕውቀትን ጠሉ።
ለሚዘልፏቸው የተመቹ ሆኑ፤
23እነሆ፥ የቃሌን መንፈስ እነግራችኋለሁ፤
ቃሌንም አስተምራችኋለሁ።
24በጠራሁ ጊዜ አልሰማችሁኝምና
እጄን ዘረጋሁ፥ ማንም አላስተዋለም#“እጄን ዘረጋሁ ማንም አላስተዋለም” የሚለው በግሪኩ የለም።
ነገርንም አበዛሁ፥ አልመለሳችሁልኝም፥
25“ምክሬን ሁሉ ናቃችሁ፥
ዘለፋዬንም አልተመለከታችሁም፥
26ስለዚህ እኔ በጥፋታችሁ እሥቃለሁ፤
ጥፋትም በመጣባችሁ ጊዜ ደስ ይለኛል።
27ጭቅጭቅ ድንገት በመጣባችሁ ጊዜ፥
እንደዚሁም ጥፋታችሁ እንደ ዓውሎ ነፋስ
በመጣባችሁ ጊዜ፥
ችግርና ምርኮ በደረሰባችሁ ጊዜ፥
እኔ ከዚያ አለሁ።
28ግን በጠራችሁኝ ጊዜ እኔ አልሰማችሁም፤
ክፉዎች ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም።
29ዕውቀትን ጠልተዋልና፥
እግዚአብሔርንም መፍራትን አልመረጡምና።
30ምክሬን ይመለከቱ ዘንድ አልፈቀዱምና፥
ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና፤
31ስለዚህ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉ፥
በራሳቸውም ኀጢአት ይጠግባሉ።
32አላዋቂዎችን አለመመለሳቸው ትገድላቸዋለችና፥
ሰነፎችንም ምርመራቸው ትገድላቸዋለች።
33የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል፥
ከክፉም ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያርፋል።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in