ኦሪት ዘኍልቍ 26
26
ሁለተኛው የእስራኤል ሕዝብ ቈጠራ
1እንዲህም ሆነ፦ መቅሠፍቱ ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2“ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጣውን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ቍጠሩ።” 3ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብለው ነገሩአቸው፦ 4“እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ከሃያ ዓመት ጀምሮ፥ ከዚያም በላይ ያለውን ሕዝብ ቍጠሩ።” ከግብፅ ምድር የወጡ የእስራኤልም ልጆች እነዚህ ናቸው።
5የእስራኤል በኵር ሮቤል፤ የሮቤል ልጆች፤ ከሄኖኅ የሄኖኃውያን ወገን፤ ከፈሉስ የፈሉሳውያን ወገን። 6ከአስሮን የአስሮናውያን ወገን፤ ከከርሚ የከርማውያን ወገን። 7እነዚህ የሮቤላውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 8የፈሉስም ልጆች፤ ኤልያብ። 9የኤልያብም ልጆች፥ ናሙኤል፥ ዳታን፥ አቤሮን፤ እነዚህም ከማኅበሩ የተመረጡ ነበሩ፤ ከቆሬ ወገን ጋር በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን ተጣሉ፤ 10ማኅበሩም በሞቱ ጊዜ ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ በዚያም ጊዜ እሳቲቱ ሁለት መቶ አምሳውን ሰዎች አቃጠለቻቸው፤ እነርሱም ለምልክት ሆኑ። 11የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም።
12የስምዖንም ልጆች በየወገናቸው፤ ከናሙሄል የናሙሄላውያን ወገን፥ ከኢያሚን የኢያሚናውያን ልጆች ወገን፥ ከያክን የያክናውያን ልጆች ወገን፥ 13ከዛራ የዛራውያን ልጆች ወገን፥ ከሳውኡል የሳውኡላውያን ወገን። 14እነዚህ የስምዖናውያን ወገኖች ናቸው፤ ቍጥራቸውም ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
15የይሁዳ ልጆች ኤርና አውናን፥ ሴሎምና ፋሬስ ዛራም፤ ዔርና አውናንም በከነዓን ምድር ሞቱ። 16የይሁዳም ልጆች በየወገናቸው፤ ከሴሎም የሴሎማውያን ወገን፥ ከፋሬስ የፋሬሳውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን። 17የፋሬስም ልጆች፤ ከኤስሮም የኤስሮማውያን ወገን፥ ከያሙሔል የያሙሔላውያን ወገን። 18እነዚህ የይሁዳ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
19የይሳኮር ልጆች በየወገናቸው፤ ከቶላ የቶላውያን ወገን፥ ከፉሓ የፉሓውያን ወገን፤ 20ከያሱብ የያሱባውያን ወገን፥ ከሥምራ የሥምራውያን ወገን። 21እነዚህ የይሳኮር ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ አራት ሺህ አራት#ዕብ. “ሦስት መቶ” ይላል። መቶ ነበሩ። 22የዛብሎን ወገኖች በየወገናቸው፥ ከሳሬድ የሳሬዳውያን ወገን፥ ከኤሎኒ የኤሎኒያውያን ወገን፥ ከያሕልኤል የያሕልኤላውያን ወገን። 23እነዚህ የዛብሎን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
24የጋድ ልጆች በየወገናቸው፤ ከሳፎን የሳፎናውያን ወገን፥ ከሐጊ የሐጋውያን ወገን፥ ከሱኒ የሱኒያውያን ወገን፤ 25ከኤዜን የኤዜናውያን ወገን፥ ከሳድፍ የሳዳፋውያን#ዕብ. “ከዔር የዔራውያን” ይላል። ወገን፤ 26ከአሮሐድ የአሮሐዳውያን ወገን፥ ከአሩሔል የአሩሔላውያን ወገን። 27እነዚህ የጋድ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አራት ሺህ#ዕብ. “አርባ ሺህ ...” ይላል። አምስት መቶ ነበሩ።
28የአሴር ልጆች በየወገናቸው፤ ከኢያምን የኢያምናውያን ወገን፥ ከኢያሱ የኢያሱያውያን ወገን፥ ከበርያ የበርያውያን ወገን። 29ከኮቤር ልጆች፤ ከከቤር የከቤራውያን ወገን፥ ከሜልክያል የሜልክያላውያን ወገን። 30የአሴርም የሴት ልጁ ስም ሳራ ነበረ። 31እነዚህ የአሴር ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ#ግሪኩና ዕብ. “አምሳ ሦስት ሺህ ...” ይላል። አራት መቶ ነበሩ።
32የዮሴፍ ልጆች በየወገናቸው፤ ምናሴና ኤፍሬም። 33የምናሴ ልጆች፤ ከማኪር የማኪራውያን ወገን፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ ከገለዓድ የገለዓዳውያን ወገን። 34የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከአክያዝር የአክያዝራውያን ወገን፥ ከኬሌግ የኬሌጋውያን ወገን፥ 35ከኢሳርያል የኢሳርያላውያን ወገን፥ ከሴኬም የሴኬማውያን ወገን፥ 36ከሲማኤር#ዕብ. “ሸሚዳ” ይላል። የሲማኤራውያን ወገን፥ ከኦፌር የኦፌራውያን ወገን። 37የኦፌርም ልጅ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዓድም የሴቶች ልጆቹ ስም መሐላ፥ ኑኃ፥ ሄግላ፥ ሚልካ፥ ቴርሳ ነበረ። 38እነዚህም የምናሴ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
39በየወገናቸው የኤፍሬም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሱቱላ የሱቱላውያን ወገን#ዕብ. “ከቤኬር የቤኬራውያን ወገን” የሚል ይጨምራል። ከጣናህ የጣናሃውያን ወገን። 40እነዚህ የሱቱላ ልጆች ናቸው፤ ከዔዴን#ዕብ. “ከኤራን” ይላል። የዔዴናውያን ወገን። 41እነዚህ የኤፍሬም ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው።
42የብንያም ልጆች በየወገናቸው፤ ከበዓሌ የበዓላውያን ወገን፥ ከአሲቤር የአሲቤራውያን ወገን፥ ከአኪራን የአኪራናውያን ወገን፥ 43ከሶፋን የሶፋናውያን ወገን፥#ዕብ. “ከሑፋም የሑፋማውያን ወገን” የሚል ይጨምራል። 44የበዓሌም ልጆች አዴርና ኖሐማን፤ ከአዴር የአዴራውያን ወገን፥ ከኖሐማን የኖሐማናውያን ወገን። 45በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
46በየወገናቸው የዳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሰምዒ፥ የሰምዒያውያን ወገን፤ በየወገናቸው የዳን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 47የሰምዒያውያን ወገኖች ሁሉ ቍጥራቸው ስድሳ አራት ሺህ#ግእዝ “ሰባ አምስት ሺህ” ይላል። አራት መቶ ነበሩ።
48የንፍታሌም ልጆች በየወገናቸው፤ ከአሴሔል የአሴሔላውያን ወገን፥ ከጎሄኒ የጎሄናውያን ወገን፥ 49ከየሴር የየሴራውያን ወገን፥ ከሴሌም የሴሌማውያን ወገን። 50በየወገናቸው የንፍታሌም ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
51ከእስራኤል ልጆች የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
52እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 53“ለእነዚህ በየስማቸው ቍጥር ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፈላለች። 54ለብዙዎቹ ብዙ ርስትን ትሰጣቸዋለህ፤ ለጥቂቶችም ጥቂት ርስትን ትሰጣቸዋለህ። ለእያንዳንዳቸው እንደ ቍጥራቸው መጠን ርስታቸውን ትሰጣቸዋለህ። 55ነገር ግን ምድሪቱ በየስማቸው በዕጣ ትከፋፈላለች፤ እንደ አባቶቻቸው ነገድ ይወርሳሉ። 56በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸውን በዕጣ ትከፍላለህ።
57የሌዊ ልጆች በየወገናቸው የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ወገን፥ ከቀዓት የቀዓታውያን ወገን፥ ከሜራሪ የሜራራውያን ወገን። 58እነዚህ የሌዊ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ የሎቢኒ ወገን፥ የኬብሮን ወገን፥ የሞሓሊ ወገን፥ የሐሙሲ ወገን፥ 59የቆሬ ወገን፥ የቀዓት ወገን። ቀዓትም እንበረምን ወለደ። በግብፅ ሀገር እነዚህን ሌዋውያንን የወለደቻቸው የሌዊ ልጅ የእንበረም ሚስት#ዕብ. “እርስዋ በግብፅ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች” ይላል። ስም ዮካብድ ነበረ። ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት። 60ለአሮንም ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛርና ኢታምር ተወለዱለት። 61በሲና በረሃ በእግዚአብሔር ፊት ከሌላ እሳት ባቀረቡ ጊዜ ናዳብና አብዩድ ሞቱ። 62ከአንድ ወርም ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉ ወንዶች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩ ሃያ ሦስት ሺህ ነበሩ። ከእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አልተሰጣቸውምና ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም።
63በሞዓብ ሜዳ ላይ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ሲቈጥሩ፥ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር የቈጠሩአቸው የእስራኤል ልጆች እነዚህ ናቸው። 64ነገር ግን ሙሴና ካህኑ አሮን በሲና ምድረ በዳ የእስራኤልን ልጆች በቈጠሩአቸው ጊዜ ከነበሩት ከእነዚያ መካከል አንድም ሰው አልነበረም። 65እግዚአብሔር ስለ እነርሱ፥ “በእውነት በምድረ በዳ ይሞታሉ” ብሎ ተናግሮአልና። ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ፥ ከነዌም ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእነርሱ አንድ ሰው ስንኳ አልቀረም። #ምዕ. 26 ከዕብ. ልዩነት አለው ፤ ምዕ. 26 ከቍ. 15 እስከ 23 በዕብ. ከቍ. 19 እስከ 27 ፤ ምዕ. 26 ከቍ. 24 እስከ 27 በዕብ. ከቍ. 15 እስከ 18 ፤ ምዕ. 26 ከቍ. 28 እስከ 31 በዕብ. ከቍ. 44 እስከ 47 ፤ ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ግእዝ ከቍ. 32 እስከ 47 ዕብ. ከቍ. 28 እስከ 43።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 26: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in