ኦሪት ዘኍልቍ 25
25
ሞዐባውያን እስራኤላውያንን በፌጎር እንደ አሳቱ
1እስራኤልም በሰጢን አደሩ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር አመነዘሩ፤ ረከሱም። 2ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም መሥዋዕታቸውን በሉ፤ ለአምላኮቻቸውም ሰገዱ። 3እስራኤልም ለብዔል ፌጎር ራሳቸውን ለዩ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ። 4እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላፈረሱ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐይ ፊት ቅጣቸው። የእግዚአብሔርም ቍጣ ከእስራኤል ይርቃል።” 5ሙሴም የእስራኤልን ሕዝቦች፥ “እናንተ እያንዳንዳችሁ ብዔል ፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ” አላቸው።
6እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ወንድሙን ወደ ምድያማዊት ሴት ወሰደው፤#ዕብ. “ምድያማዊቱን ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት” ይላል። እነርሱም በምስክሩ ድንኳን ዳጃፍ ያለቅሱ ነበር። 7የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ። 8ያንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። ሁለቱንም እስራኤላዊውን ሰውና ምድያማዊቱን ሴት ሆዳቸውን ወጋቸው፤ ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተወገደ። 9በመቅሠፍቱም የሞቱት ሃያ አራት ሺህ ነበሩ።
10እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11“የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። 12ስለዚህ አልሁ፦ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ። 13ለአምላኩ ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና፥ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም የክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።”
14ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። 15የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም የምድያም አባቶች ወገን የሚሆን የሳሞት ወገን አለቃ ነበረ።
16እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ 17ምድያማውያንን አስጨንቋቸው፤ ግደሉአቸውም። 18ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 25: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in