YouVersion Logo
Search Icon

ትን​ቢተ ሚክ​ያስ 2

2
1በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ኃይል በእጃቸው ነውና ሲነጋ ይፈጽሙታል።
2በእርሻው ላይ ይመኛሉ፥ በግዴታም ይይዙታል፥ በቤቶችም ላይ ይመኛሉ፥ ይወስዱአቸውማል፥ ሰውንና ቤቱን፥ ሰውንና ርስቱንም ይነጥቃሉ።
3ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህ ወገን ላይ በክፉ አስባለሁ፥ ከዚያም አንገታችሁን አታነሡም፥ ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም።
4በዚያ ቀን በምሳሌ ይመስሉባችኋል፥ በጽኑ ልቅሶም ያለቅሱላችኋል፥ እነርሱም፦ ፈጽመን ጠፍተናል፥ የሕዝቤን እድል ፈንታ ይሰፍራል፥ እርሱንም የሚከለክል የለም፥ እርሻችንን ለዓመፀኞች ይከፍላል ይላሉ።
5ስለዚህ በእግዚአብሔር ጉባኤ መካከል በዕጣ ገመድ የሚጥል አይኖርህም።
6ትንቢት አትናገሩ ብለው ይናገራሉ፥ በእነዚህ ላይ ትንቢት አይናገሩም፥ ስድብም አይርቅም።
7የያዕቆብ ቤት የተባልህ ሆይ፥ በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ የማይታገሥ ነውን? ወይስ ሥራው እንደዚያች ናትን? ቃሌስ በቅን ለሚሄድ በጎነት አያደርግምን?
8ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቤ እንደ ጠላት ሆኖ ተነሥቶአል፥ ቀሚስንና መጐናጸፊያን ገፈፋችሁ፥ ሳይፈሩም፥ የሚያልፉትን ከሰልፍ እንደሚመለሱ አደረጋችኋቸው።
9የሕዝቤንም ሴቶች ከተሸለሙ ቤቶቻቸው አሳደዳችኋቸው፥ ከሕፃናቶቻቸውም ክብሬን ለዘላለም ወሰዳችሁ።
10በዚህ ዕረፍት የላችሁምና ተነሥታችሁ ሂዱ፥ በርኵሰት ምክንያት ክፉ ጥፋት ታጠፋችኋለች።
11ነፋስንም ተከትሎ፦ ስለ ወይን ጠጅና ስለ ስካር ትንቢት እናገርልሃለሁ ብሎ ሐሰትን የሚናገር ሰው ቢኖር እርሱ ለዚህ ሕዝብ ነቢይ ይሆናል።
12ያዕቆብ ሆይ፥ ሁልንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፥ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፥ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
13ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፥ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጥተዋል፥ ንጉሣቸውም በፊታቸው አልፎአል፥ እግዚአብሔርም በራሳቸው ላይ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in