YouVersion Logo
Search Icon

ትን​ቢተ ሚክ​ያስ 1

1
1በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙ፥ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፥ ጌታ እግዚአብሔርም፥ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፥ ይመስክርባችሁ።
3እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል።
4ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ፥ በበታቹ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ።
5ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
6ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፥ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።
7የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖታትዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፥ በግልሙትና ዋጋ ሰበሰባቻቸው፥ ወደ ግልሙትናም ዋጋ ይመለሳሉና።
8ስለዚህ ነገር ዋይ ብላ ታለቅሳለች፥ ባዶ እግርዋንና ዕራቁትዋን ሆና ትሄዳለች፥ እንደ ቀበሮ ታለቅሳለች፥ እንደ ሰጐንም ዋይ ትላለች፥
9ቁስልዋ የማይፈወስ ነውና፥ እስከ ይሁዳም ደርሶአልና፥ ወደ ሕዝቤም በር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦአልና።
10በጌት ላይ አታውሩ፥ በአኮ ላይ እንባን አታድርጉ፥ በቤትዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።
11በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በዕራቁትነትሽና በእፍረት እለፊ፥ በጸዓናን የምትቀመጠው አልወጣችም፥ የቤትኤጼል ልቅሶ ከእናንተ ዘንድ መኖሪያውን ይወስዳል።
12ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአልና በማሮት የምትቀመጠው በጎነትን ትጠባበቃለች።
13በለኪሶ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሰረገላውን ለፈረስ እሰሪ፥ እርስዋ ለጽዮን ሴት ልጆች የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፥ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና።
14ስለዚህ ትሎት ለሞሬሼትጌት ትሰጪአለሽ፥ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት አታላይ ይሆናሉ።
15በመሪሳ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፥ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዶላም ይመጣል።
16ተማርከው ከአንቺ ዘንድ ወጥተዋልና ስለ ተድላሽ ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ጠጕርሽንም ተቈረጪ፥ ቡሃነትሽንም እንደ ንስር አስፊ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in