መጽሐፈ ኢዮብ 30
30
ምዕራፍ 30።
1“አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ ለመዘባበት በእኔ ላይ ሳቁ፤
አባቶቻቸውን የናቅሁባቸውና እንደ መንጋዬ ውሾች ያልቈጠርኋቸው
ዛሬ ለብቻቸው ይገሥጹኛል።
2የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምንድን ነው?
ሞት በላያቸው ይምጣ።
3ትላንት በድካምና በውርደት ከምድረ በዳ ያመለጡ፥
ከረኃብ የተነሣ ተሰድደው ይለምናሉ።
4እየዞሩ የሚለምኑና የሚበሉ#ከግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩነት አለው።
በቅልውጥም የሚኖሩ ወራዶች፥
ዐመፀኞችና ከበጎ ነገሮች ሁሉ የተቸገሩ ናቸው።
ከታላቅ ረኃብም የተነሣ ጨው ጨው የሚለውን የእንጨት ሥር ይበላሉ።
5“ሌቦች በእኔ ላይ ተነሡ፥
6በሸለቆው ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ ውስጥ
በዓለትም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ፤
7በገደል ማሚቶው መካከል ይጮኻሉ፤
በሳማ ውስጥም ይሸሸጋሉ።
8የሰነፎችና የክፉዎች ሰዎች ልጆች ናቸው፤
ስማቸውና ክብራቸው ከምድር የጠፋ ነው።
9አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው።
10ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤
ምራቃቸውንም በፊቴ መትፋትን አልታከቱም።
11የቀስቱን አፎት ከፍቶ ክፉ አደረገብኝ፤
በፊቴም ልጓሙን ሰደደ።
12በኀይሉ ቀኝ ተነሣብኝ፤
እግሮቹንም ዘረጋብኝ፤
የሞትንም መንገድ በእኔ ላይ አደረገ።
13ፍለጋዬን አጠፋ፤
ልብሴን ገፈፈኝ፥ በቀስቱም ነደፈኝ።
14እንደ ወደደ አደረገብኝ፤#ምዕ. 30 ከቍ. 12 እስከ 14 በብዙ የሚያደርግ ዘርዕ አለ።
በመከራም እዛብራለሁ።
15ድንጋጤ በላዬ ተመላለሰችብኝ፥
ነፍሴ ከእኔ ላይ እለይ እለይ አለች፥
ደኅንነቴም እንደ ተበተነ ደመና አለፈች።
16“አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤
ጭንቀትም በእኔ ላይ ሞላ፤
17በሌሊት ሁሉ አጥንቶች በደዌ ይነድዳሉ፥
ጅማቶችም ይቀልጣሉ።
18ከታላቁ ደዌ ኀይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤
የልብሴ ክሳድ አነቀችኝ፥
ቀሚሴም በአንገቴ ተጣበቀ።
19እርሱ እንደ ጭቃ ረገጠኝ፥
ዕድል ፋንታዬም አፈርና አመድ ሆነ።
20ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልሰማኸኝምም፤
እነርሱ ግን ቆመው ተመለከቱኝ።
21ምሕረት የሌላቸው ሰዎች ደበደቡኝ፥
የገረፈችኝ እጅም በረታች።
22በኀዘን አኖርኸኝ፥
ከሕይወቴም አራቅኸኝ።
23ሞት እንደሚያጠፋኝ አውቃለሁና
ለሟችም ሁሉ ማደሪያው ምድር ናትና።
24እኔ ራሴ ልታነቅ በወደድሁ ነበር
ይህም ባይሆን ሌላው እንዲሁ እንዲያደርግልኝ እለምናለሁ።
25ረዳት ለሌለው ሰው አለቀስሁ
የተቸገረ ሰውን ባየሁ ጊዜ ጮኽሁ።
26ነገር ግን በጎ ነገርን በተጠባበቅኋት ጊዜ
እነሆ ክፉ ቀኖች መጡብኝ፤
ብርሃንን ተስፋ አደረግሁ፥ ጨለማም መጣብኝ።#በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
27ሆዴ ፈላች፥ አላረፈችምም፤
የችግርም ዘመን መጣችብኝ።
28በጠባቡ ሄድሁ፥ የሚያሰፋልኝም አጣሁ፥
በጉባኤም መካከል ቆሜ እጮኻለሁ።
29ለሌሊት ዎፍ ወንድም፥#ዕብ. “አክይስት” ይላል።
ለሰጎንም ባልንጀራ ሆንሁ።
30ቍርበቴ እጅግ ጠቈረ፥
አጥንቶቼም ከትኩሳት የተነሣ ተቃጠሉ።
31ስለዚህ ሕማሜ መሰንቆ፥
ልቅሶዬም በገና ሆነብኝ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 30: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in