ትንቢተ ሕዝቅኤል 14
14
ጣዖት አምላኪዎች እንደ ተወገዙ
1ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ#“አያሌ” የሚለው በዕብ. ብቻ። ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። 2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3“የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች በልባቸው ጣዖቶቻቸውን አኑረዋል፤#ዕብ. “ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል” ይላል። የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ለእነርሱ መልስ ልመልስላቸውን? 4ስለዚህ ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ ቢመጣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። 5ይህም የእስራኤልን ወገኖች በዐሳባቸው ከእኔ እንደ ተለዩበት እንደ ልባቸውና እንደ ርኵሰታቸው ያስታቸው ዘንድ ነው።”
6ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሓ ግቡ፤ ከበደላችሁም#ዕብ. “ከጣዖታችሁ” ይላል። ተመለሱ፤ ፊታችሁንም ከኀጢአታችሁ ሁሉ መልሱ። 7ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ። 8ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ፤ እንዲጠፋም#ዕብ. “ምልክትና ምሳሌ” ይላል። አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 9ነቢዩም ቢታለል፥ ቃልንም ቢናገር፥ ያን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ። 10ኀጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ እንደሚጠይቀውም ሰው ኀጢአት እንዲሁ የነቢዩ ኀጢአት ይሆናል። 11ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ፥ በኀጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው፤ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
12የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13“የሰው ልጅ ሆይ! ምድር ብትበድለኝ፥ ብትስት፥ ኀጢአትም ብትሠራ እጄን በእርስዋ አነሣለሁ፤ የእህሉንም ኀይል አጠፋለሁ፤ በእርስዋም ረሀብን እልካለሁ፤ ከብቱንና ሰዉንም ከእርስዋ አጠፋለሁ። 14እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም በመካከልዋ ቢኖሩ በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ያድናሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15በዚያች ሀገር ላይ ክፉ አውሬን ባመጣ፥ ፈጽሜም ባጠፋት በዚያም አውሬ ፊት የሚያልፍ ባይገኝ፥ 16እነዚህ ሦስት ሰዎች በመካከልዋ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝ! እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፤ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ፦ ሰይፍ ሆይ! በምድሪቱ ላይ እለፊ ብል፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ባጠፋ፥ 18እነዚህ ሦስት ሰዎች በመካከልዋ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝ! እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈርን ብሰድድ፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ መዓቴን በደም ባፈስስባት፥ 20ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም በመካከልዋ ቢኖሩ፤ እኔ ሕያው ነኝ! በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፥ “ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ መቅሠፍቶችን፥ ሰይፍንና ራብን፥ ክፉዎችንም አውሬዎች፥ ቸነፈርንም ስሰድድባት፥ 22ነገር ግን እነሆ የሚያመልጡና ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ከእርስዋ የሚያወጡ ይቀሩላታል፤ እነሆ ወደ እናንተ ይወጣሉ፤ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ፤ 23መንገዳቸውንና ሥራቸውን በአያችሁ ጊዜ ያጽናኗችኋል፤ ያደረግሁባትንም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁባት ታውቃላችሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 14: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in