መጽሐፈ ባሮክ 1
1
1የኬልቅዩ ልጅ የአሳድዩ ልጅ የሴዴቅያስ ልጅ የማሴው ልጅ የኔርዩ ልጅ ባሮክ ወደ ባቢሎን የጻፈው ነገር ይህ ነው፤ 2በአምስተኛው ዓመት ከወሩ በሰባተኛው ቀን ከለዳውያን ኢየሩሳሌምን በያዙአትና በእሳት በአቃጠሏት ጊዜ፥ 3ባሮክ ይህን መጽሐፍ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ጆሮና መጽሐፉን ለመስማት ከሕዝቡ ዘንድ ወደ እርሱ በመጣው ሕዝብ ሁሉ ጆሮ፥ 4በኀያላኑና በልዑላኑ ጆሮ፥ በሽማግሌዎች ጆሮና ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በባቢሎን በሶዲ ወንዝ አጠገብ በሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ጆሮ አነበበ። 5እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ ጾሙ፤ ጸለዩም። 6እያንዳንዳቸውም እንደ እየችሎታቸው ገንዘብ ሰበሰቡ፤ 7እርሱንም ወደ ሰሉም ልጅ ወደ ኬልቅያ ልጅ ወደ ካህኑ ኢዮአቄም፥ በኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ወደ ነበሩት ካህናትና ወደ ሕዝቡ ሁሉ ላኩት። 8ከቤተ መቅደስ የተወሰደውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ወደ ይሁዳ ምድር ይመልሱ ዘንድ በሲባን ወር በዐሥረኛው ቀን በወሰዱ ጊዜ ይህም ዕቃ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ ያሠራው የብር ዕቃ ነበር። 9ይኸውም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢኮንያንንና መኳንንቱን፥ ምርኮኞቹንና ኀያላኑን የሀገሩንም ሕዝብ ይዞ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ከወሰዳቸው በኋላ ነበር።
ወደ ኢየሩሳሌም የተጻፈ ደብዳቤ
10እንዲህም አሉ፥ “እነሆ ገንዘብ ልከንላችኋል፤ በእርሱም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት፤ ዕጣንም ግዙበት፤ ኅብስትም አዘጋጁ፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያም አቅርቡ። 11ዘመናቸው በምድር ላይ እንደ ሰማይ ዘመን ይሆን ዘንድ ስለ ባቢሎን ንጉሥ ስለ ናቡከደነፆር ሕይወትና ስለ ልጁ ስለ ብልጣሶር ሕይወት ጸልዩ። 12ለእኛም እግዚአብሔር ኀይልን ይሰጠን ዘንድ፥ ዐይኖቻችንንም ያበራልን ዘንድ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ጥላ ሥርና በልጁ በብልጣሶር ጥላ ሥር በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ለብዙ ዘመንም እንገዛላቸው ዘንድ፥ በፊታቸውም ባለሟልነትን እናገኝ ዘንድ ጸልዩ። 13አምላካችንን በድለናልና፤ የእግዚአብሔርም መዓቱ መቅሠፍቱም እስከዚች ቀን ድረስ ከእኛ አልተመለሰችምና ለእኛም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን። 14ወደ እናንተ የላክናትን ይህችንም ደብዳቤ አንብቡአት፤ በበዓል ቀንና በተወደደውም ዕለት በእግዚአብሔር ቤት ተናዘዙ።
የኀጢአት ኑዛዜ
15“እንዲህም በሉ፤ ጽድቅ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ ለእኛ ግን ለፊታችን ኀፍረት ነው፤ ይህች ቀን ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ፥ 16ለንጉሦቻችንና ለአለቆቻችን፥ ለካህኖቻችንና ለነቢያቶቻችን፥ ለአባቶቻችንም ኀፍረት እንደ ሆነች። 17በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት በድለናልና፤ 18አልታዘዝነውምና የአምላካችን የእግዚአብሔርንም ቃል አልሰማንምና፤ በሰጠን በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ አልሄድንምና፤ 19አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ከአወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ አምላካችንን እግዚአብሔርን አልታዘዝነውም፤ ቃሉንም እንዳንሰማ ከእርሱ ራቅን። 20ወተትና መዓር የምታፈስሰውን ምድር ይሰጠን ዘንድ አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር በአወጣበት ቀን እግዚአብሔር ለባሪያው ለሙሴ ያዘዘው ይህ ክፉ ነገርና መርገም እንደ ዛሬው ዕለት አገኘን። 21ወደ እኛ እንደ ላካቸው እንደ ነቢያት ቃል የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንም። 22በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ እናደርግ ዘንድ ለባዕዳን አማልክት እየተገዛን እያንዳንዳችን በክፉ ልባችን ፈቃድ ሄድን።
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 1: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in