ትንቢተ አሞጽ 6
6
የእስራኤል ቅጣት
1ጽዮንን ለሚንቁ፥ በሰማርያም ተራራ ለሚታመኑ ሰዎች ወዮላቸው፤ የአሕዛብን አለቆች ለቀሙአቸው። 2የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ወደ ካልኔ ተሻግራችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ኤማትራባ እለፉ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይበረታሉ፤ ድንበራቸውም ከድንበራቸው ይሰፋልና። 3ክፉ ቀንን ለሚፈልጓት፥ የሐሰት ሰንበታትን ለሚያቀራርቡና አንድ ለሚያደርጉ፥#ዕብ. “ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፥ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ” ይላል። 4ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለሚተኙ፥ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን፥ ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ፥ 5ከበገናው ድምፅ ጋር#ዕብ. “ከዳዊት በገና ጋር” ይላል። አስተባብረው ለሚያጨበጭቡ ሰዎች፤ ይኸውም የማያልፍ ለሚመስላቸውና እንደሚያመልጣቸው ለማያውቁ፤ 6በጽዋ የቀላ ወይን ለሚጠጡ፥ እጅግ በአማረ ሽቱም ለሚቀቡ፥ በዮሴፍ ስብራት ለማያስቡ ወዮላቸው።
7ስለዚህ ከአለቆቻቸው አስቀድመው ይማረካሉ፤ ሯጮች የሚሆኑ የኤፍሬም ፈረሶችም ያልቃሉ። 8ጌታ እግዚአብሔር፥ “የያዕቆብን ትዕቢት አረክሳለሁ፤ ሀገሮቹንም ጠላሁ፤ ከተሞቹንም ከሚኖሩባቸው ሰዎች ጋር አጠፋለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአልና። 9እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ፤ የቀሩት ግን ይተርፋሉ።#“የቀሩት ግን ይተርፋሉ” የሚለው በዕብ. የለም። 10አጥንቶቻቸውንም ከቤት ያወጡ ዘንድ ቤተሰቦቻቸው በወሰዱአቸው ጊዜ፥ ቤት ጠባቂውን በአንተ ዘንድ የቀረ አለን? በአለው ጊዜ እርሱ የለም ይላል። ያም የእግዚአብሔርንም ስም እንዳትጠራ ዝም በል ይለዋል። 11እነሆም እግዚአብሔር ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። 12ፍርድን ወደ ቍጣ፥ የእውነትንም ፍሬ ወደ እሬት ለውጣችኋልና፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን?#ግእዝ “ወያረምሙኑ እምአንስት” ይላል። 13በከንቱ ነገር ደስ የሚላችሁ በኀይላችን ቀንዶችን አበቀልን የምትሉ አይደለምን? 14“የእስራኤል ቤት ሆይ እነሆ እኔ የሚያስጨንቋችሁን ሕዝብ አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፤ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዐረባ ወንዝ ድረስ ትገቡ ዘንድ አይፈቅዱላችሁም።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 6: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in