ትንቢተ አሞጽ 5
5
የንስሓ ጥሪ
1የእስራኤል ቤት ሆይ! በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 2የእስራኤል ድንግል ወደቀች፤ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ተጣለች፤ የሚያስነሣትም የለም። 3ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና፥ “ሺህ ከሚወጡባት ከተማ መቶ ይቀራሉ፤ መቶም ከሚወጡባት ከተማ ለእስራኤል ቤት ዐሥር ይቀራሉ።”
4እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና፥ “እኔን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ 5ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም እንዳልነበረች ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፤ ወደ ጌልገላም አትሂዱ፤ ወደ ቤርሳቤህም#“ዓዘቅተ መሐላ” ማለት ነው። አትለፉ።” 6በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ እንዳትበላቸውም የእስራኤልንም ቤት እሳት የሚያጠፋላቸው እንዳያጡ#ዕብ. “በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ” ይላል። እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ። 7እግዚአብሔር ፍርድን በሰማይ ያደርጋል፤ ጽድቅንም በምድር ላይ ይመሠርታል።#ዕብ. “ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጻድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ” ይላል። 8ሁሉን የሚሠራና የሚያቅናና፥ ብርሃኑን ወደ መስዕ የሚመልሰው፥ ቀኑን እንደ ሌሊት የሚያጨልመው፥#ዕብ. “ሰባቱን ከዋክብትና ኦርዮን የተባለውን ኮከብ የፈጠረውን፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጠውን” ይላል። የባሕሩንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት የሚያፈስሰው ስሙ ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር ነው። 9በኀያላን ላይ ቅጥቃጤን፥ በአንባዎችም ላይ ጕስቍልናን ያመጣል።
10በበሩ የሚገሥጸውን ጠሉ፤ እውነትንም የሚናገረውን ተጸየፉ። 11ድሃውንም ደብድባችኋልና፤ መማለጃንም#ዕብ. የስንዴውንም ቀረጥ” ይላል። ከእርሱ ወስዳችኋልና፤ ያማሩ ቤቶችንም መርጣችሁ#ዕብ. “ከተጠረበ ድንጋይ” ይላል። ሠርታችኋልና፥ ነገር ግን አትኖሩባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎችም ተክላችኋል፤ ነገር ግን ወይንን አትጠጡም። 12ጻድቁን የምታስጨንቁ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም የችግረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ! በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኀጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ ዐውቃለሁና። 13ስለዚህ ዘመኑ ክፉ ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ ዝም ይላል።
14በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን ፈልጉ፤ ክፉውንም አይደለም፤ እንዲሁ እናንተ እንደ ተናገራችሁ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል። 15ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ለዮሴፍ ቅሬታ ይራራ ይሆናል።
16ስለዚህ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በየአደባባዩ ሁሉ ላይ ዋይታ ይሆናል፤ በየመንገዱም ሁሉ ላይ ወዮ ወዮ ይባላል፤ ገበሬዎቹም ወደ ልቅሶ፥ አልቃሾቹም ወደ ዋይታ ይጠራሉ። 17በመካከልህ አልፋለሁና በጎዳናው#ዕብ. “በወይን ቦታ” ይላል። ሁሉ ልቅሶ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር።
የእግዚአብሔር ቀን
18የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም። 19ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ፥ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወደ ቤትም ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ይሆናል። 20የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?
21ዓመት በዓላችሁን ጠልችዋለሁ፤ አርቄውማለሁ፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “በጉባኤያችሁም የመሥዋዕታችሁን መዓዛ አላሸትም” ይላል። መዓዛ መሥዋዕታችሁን አላሸትም።#ዕብ. “የተቀደሰውም ጉባኤያችሁ ደስ አያሰኝም” ይላል። 22የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁንና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ የድኅነት መሥዋዕታችሁንም#ዕብ. “ለምስጋና የምታቀርቡልኝ የሰቡትን እንስሶች” ይላል። አልመለከትም። 23የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላዳምጥም። 24ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ።
25“የእስራኤል ቤት ሆይ! በውኑ በምድረ በዳ አርባ ዓመት ሙሉ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኛልን? 26ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎች፥ የሞሎክን ድንኳንና የአምላካችሁን የሬፋንን ኮከብ አነሣችሁ። 27ስለዚህ ከደማስቆ ወደዚያ አስማርካችኋለሁ” ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የተባለ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 5: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in