መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 9
9
እግዚአብሔር ለሰሎሞን ዳግመኛ እንደ ተገለጠለት
(2ዜ.መ. 7፥11-22)
1ከዚህም በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን ያደርገው ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ 2እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። 3እግዚአብሔርም አለው፥ “በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ እንደ ጸሎትህም ሁሉ አደረግሁልህ፤ ለዘለዓለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዐይኖችና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። 4ዳዊትም አባትህ በጽድቅ፥ በንጹሕ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዐቴንም ሕጌንም ብትጠብቅ፥ 5እኔ፦ በእስራኤል ላይ የሚገዛ ሰውን ከአንተ አላጠፋም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ። 6ነገር ግን እናንተና ልጆቻችሁ እኔን ትታችሁ ወደ ኋላ ብትመለሱ ለሙሴ በፊታችሁ የሰጠሁትን ትእዛዜንና ሥርዐቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ 7እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ለጥፋትና ለተረት ይሆናሉ። 8ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ፦ እግዚአብሔር በዚህ ሀገርና በዚህ ቤት ስለ ምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። 9መልሰውም፦ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።”#የምዕ. 9 ቍ. 9 የመጨረሻው ዐረፍተ ነገር በዕብ. የለም። ያንጊዜም ሰሎሞን የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ በዚያ ወራት ለራሱ በሠራው ቤት አስገባት። 10ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች በሠራበት በሃያ ዓመት ውስጥ፥ 11የጢሮስ ንጉሥ ኪራም በዝግባና በጥድ እንጨት፥ በወርቅና በሚሻውም ሁሉ ሰሎሞንን ረድቶት ነበር። ያንጊዜም ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሃያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። 12ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ወደ ገሊላም ሄደ፤#“ወደ ገሊላም ሄደ” የሚለው በዕብ. የለም። ደስም አላሰኙትም። 13እርሱም አለው፥ “ወንድሜ ሆይ! የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድን ናቸው?” እስከ ዛሬም ድረስ ወሰን ብሎ ጠራቸው። 14ኪራምም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ለሰሎሞን አመጣ።
15ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና ቤተ መንግሥቱን፥ ሜሎንንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ አሶርንም፥ መጊዶንም፥ ጋዜርንም ይሠራ ዘንድ ሠራተኞችን መልምሎ ነበር። 16የግብፅም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጋዜርን ያዘ፤ በእሳትም አቃጠላት፤ በሜርጎብ#ዕብ. “በከተማ” ይላል። ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንንም ገደላቸው፤ ለልጁም ለሰሎሞን ሚስት እነዚያን አገሮች ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር። 17ሰሎሞንም ጋዜርንና የታችኛውን ቤቶሮንን፥ ባዕላትንም ሠራ፤ 18በምድረ በዳ ሀገር ያለችውን ኤያቴርሞትን ሠራ፤ 19ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፤ የሰረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም፥ በሊባኖስም፥ በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ። 20ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞሬዎናውያንና ከኬጤዎናውያን፥ ከከናኔዎን፥ ከፌርዜዎናውያን፥ ከኤዌዎናውያን፥ ከኢያቡሴዎናውያንና ከጌርጌሴዎናውያን፥ የቀሩትን አሕዛብ ሁሉ፥ ከእነርሱም በኋላ በምድሪቱ የቀሩትን፥ 21የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ ልጆቻቸውን ሰሎሞን እሰከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 22ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ገባር አላደረገም፤ እነርሱ ግን ተዋጊዎች፥ ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሰረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ። 23ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
24የፈርዖንንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤቷ አመጣት፤ በዚያ ጊዜም ሚሎንን ሠራት።
25ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የሰላሙን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ።
26ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤላት አጠገብ ባለችው በጋሴዎንጋቤር መርከቦችን ሠራ። 27ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን አገልጋዮች ጋር ባሕሩን መቅዘፍ የሚያውቁ መርከበኞች አገልጋዮቹን ላከ። 28ወደ አፌርም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሶፌራ” ይላል። ደረሱ፤ ከዚያም አራት መቶ ሃያ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “መቶ ሃያ” ይላል። መክሊት ወርቅ ወሰዱ፤ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞንም ይዘው አገቡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 9: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in