መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 10
10
ንግሥተ ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገችው ጕዞ
(2ዜ.መ. 9፥1-12)
1የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፥ የእግዚአብሔርንም ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። 2በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ ነገረችው። 3ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ያልተረጐመላትና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። 4የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ 5የሰሎሞንንም የማዕዱን መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም ሥርዐት፥ አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያቀርበውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ተደነቀች። 6ንጉሡን ሰሎሞንንም አለችው፥ “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በሀገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 7እኔም መጥቼ በዐይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር ፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ በሀገሬ ሳለሁ ከነገሩኝ ይልቅ የበለጠ መልካም ተጨማሪ አየሁ። 8ሚስቶችህ የተመሰገኑ ናቸው፤ በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ፥ ጥበብህን የሚሰሙ እነዚህ አገልጋዮችህም ምስጉኖች ናቸው። 9አንተን በእስራኤል ዙፋን ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደ አምላክህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘለዓለም ያጸናው ዘንድ ወድዶታልና ስለዚህ በየነገራቸው ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ።” 10ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቶ፥ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቶ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር።
11ከኦፌርም ወርቅ ያመጣች የኪራም መርከብ እጅግ ብዙ የተጠረበ እንጨትና የከበረ ዕንቍ አመጣች። 12ንጉሡም ከተጠረበው እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በምድር ላይ እንደዚያ ያለ የተጠረበ እንጨት ከቶ አልመጣም፤ በየትም ቦታ አልታየም።
13ንጉሡም ሰሎሞን በእጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ፥ ከእርሱም የጠየቀችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ የከለከላትም የለም፤ እርስዋም ተመልሳ ከአገልጋዮችዋ ጋር ወደ ሀገርዋ ሄደች። 14በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 15ይኽንም፥ ግብር የሚያስገብሩ ሰዎች፥ ነጋዴዎችም፥ በዙሪያው ያሉ#ዕብ. “የዓረብ ነገሥታት” ይላል። ነገሥታትም ሁሉ፥ የምድርም ሹሞች ከሚያወጡት ሌላ ነው። 16ንጉሡ ሰሎሞንም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ#ዕብ. “ስድስት መቶ” ይላል። አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ#ዕብ. “ስድስት መቶ” ይላል። ሰቅል ነበረ። 17ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነው፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 18ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። 19ወደ ዙፋንም የሚያስኬዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በላም ምስል የተቀረጸ በወዲህና በወዲያም መደገፊያ ነበረው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ 20በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 21ንጉሡም ሰሎሞን ያሠራው የመጠጫ ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፤ ኵስኵስቱም የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር የተባለውን የዚያን ቤት ዕቃ ሁሉ በወርቅ አስለበጠው። የብርም ዕቃ አልነበረም፤ በሰሎሞን ዘመን የብር ዋጋ ዝቅተኛ ነበርና። 22ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር በባሕር ውስጥ የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በየሦስት ዓመትም አንድ መርከብ ከተርሴስ ወርቅና ብር፥ የተቀረጸና የተደረደረ ዕንቍ ይዞ ይመጣ ነበር።
23ንጉሡም ሰሎሞን በብልጥግናና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ እጅግ በልጦ ነበር። 24የምድርም ነገሥት#ዕብ. “ምድር ሁሉ” ይላል። ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ለማየት ይሹ ነበር። 25እነርሱም ሁሉ በዓመት በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥#“የጦር መሣሪያ” የሚለው በግእዝና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎዎች እየያዙ ይመጡ ነበር።
26ሰሎሞንም ለሰረገሎቹ ዐራት ሺህ እንስት ፈረሶች ነበሩት፤ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞችም ነበሩት፤ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው።#የምዕ. 10 ቍ. 26 የመጨረሻው ዐረፍተ ነገር በዕብ. የለም። ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ድንበር ድረስ በነገሥታቱ ሁሉ ላይ ንጉሥ ነበር። 27ንጉሡም ብሩንና ወርቁን#“ወርቅ” የሚለው በዕብ. የለም። በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቆላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 28ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብፅና ከቴቁሄ ሀገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቴቁሄ ያመጡአቸው ነበር። 29አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በአንድ መቶ” ይላል። አንዱም ፈረስ በመቶ ኀምሳ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኀምሳ” ይላል። ብር ከግብፅ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጤዎናውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በባሕሩ በኩል ያወጡላቸው ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 10: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in