መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 14
14
1በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ እጅግ ታመመ። 2ኢዮርብዓምም ሚስቱ ሐኖንን፥ “ተነሺ፥ ራስሽን ለውጪ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ ማንም አይወቅ፤ ወደ ሴሎም ሂጂ፤ ስለዚህም ሕፃን ከደዌው ይድን እንደሆነ ጠይቂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደምነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ። 3በእጅሽም ለእግዚአብሔር ሰው ዐሥር እንጀራና የወይን እሸት አንድም ማሠሮ ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል” አላት። 4የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፤ ተነሥታም እንጀራ፥ የወይን ዘለላና አንድ ማሠሮ ማር በመያዝ ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት ገባች። አኪያ ግን ስለ መሸምገሉ ዐይኖቹ ፈዝዘው ነበርና ማየት አልቻለም። 5እግዚአብሔርም አኪያን፥ “እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ራስዋንም ለውጣ ወደ አንተ በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት” አለው።
6እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፤ እንዲህም አላት፥ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ፥ ግቢ! ስለምንስ ራስሽን ለወጥሽ? እኔም የሚያስጨንቅ ወሬ ይዤ ወደ አንቺ ተልኬአለሁ። 7ሂጂ ለኢዮርብዓም እንዲህ በዪው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይም ንጉሥ አድርጌህ ነበር። 8ከዳዊትም ቤት፤ መንግሥቱን ከፍዬ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም። 9ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቈጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፤ ወደ ኋላህም ተውኸኝ። 10ስለዚህ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራን አመጣለሁ፤ ኢዮርብዓምንም አጠፋዋለሁ፤ አጥር ተጠግቶ እስከሚሸን ወንድ ድረስ አላስቀርለትም፤ በእስራኤልም ላይ ይነግሥ ዘንድ አልተወውም፤ ሰው ገለባ እስኪያልቅ ድረስ እንደሚያነድድ በኢዮርብዓም ቤት ላይ እሳትን አነዳለሁ። 11እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ከኢዮርብዓም ወገን በከተማዪቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል። 12እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጅሽ ይሞታል። 13ደንገጡሮችሽም ሊቀበሉሽ ይወጣሉ፤ ልጅሽም ሞተ ይሉሻል፥#“ደንገጥሮችሽም ሊቀበሉሽ ይወጣሉ ልጅሽም ሞተ ይሉሻል” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፤ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል። 14እግዚአብሔር ደግሞ የኢዮርብዓምን ቤት የሚያጠፋ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ያነግሣል፤ እርሱም ዛሬ ይደረጋል፤ እንግዲህ ወዲህ ምን እናገራለሁ? 15በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውኃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ አፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፤ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል። 16ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኀጢአት እስራኤልን ይጥላል።”
17የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፤ ወደ ቴርሳም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሳሪራ” ይላል። መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ። 18በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት፥ አለቀሱለትም።
19የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሃያ አራት#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሃያ ሁለት” ይላል። ዓመት ነበረ፥ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፥ ልጁም ናባጥ#ዕብ. “ናዳብ” ይላል። በፋንታው ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም
(2ዜ.መ. 11፥5—12፥15)
21የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፥ እርስዋም አሞናዊት ነበረች። 22ሮብዓምም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቹ በሠሩት ኀጢአትና በደል ሁሉ እንደ አስቀኑት በሠራው ኀጢአት አስቀናው። 23እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችን ሠሩ፤ ሐውልቶችንና የማምለኪያ አፀዶችንም ለራሳቸው አቆሙ። 24በምድርም ሁሉ ዐመፅ ነበረ፥#ዕብ. “በምድር ውስጥ ሰዶማውያን ነበሩ” ይላል። ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸው የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር።
25ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሱስቀም በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። 26የእግዚአብሔርን ቤተ መዛግብትና የንጉሡን ቤተ መዛግብት ሁሉ ወሰደ፤ ዳዊትም ከሱባ ንጉሥ ከአድርዓዛር ልጆች እጅ ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸውን የወርቅ ጦሮችና ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻና ጦር ሁሉ ወደ ግብፅ ወሰደ። 27ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፤ በፊቱም ለሚሮጡና የንጉሥን ቤት ደጅ ለሚጠብቁ የዘበኞች አለቆች ሰጣቸው። 28ከዚህ በኋላ ንጉሡ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር።
29የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ እነሆ፥ ተጽፎአል። 30በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበረ። 31ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያ በፋንታው ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 14: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in