መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 11
11
ሰሎሞን ከእግዚአብሔር እንደ ራቀ
1ንጉሡም ሰሎሞን ሴቶችን ይወድ ነበር፥ ከባዕዳን ሕዝብም የፈርዖንን ልጅ፥ ሞዓባውያትንና አሞናውያትን፥ ሶርያውያትንና ሲዶናውያትን፥ ኤዶማውያትንና አሞሬዎናውያትንም፥ ኬጤዎናውያትንም፦ ሚስቶችን አገባ። 2እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች፥ “አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን እንዳይመልሱ ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ” ካላቸው ከአሕዝብ አገባ፤ ሰሎሞን ግን እነርሱን ተከተለ፤ ወደዳቸውም። 3ለእርሱም ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት። 4ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ልቡ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር አልነበረም። ከባዕድ ያገባቸው ሚስቶቹም ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን መለሱት። 5ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስጠራጢስን የአሞናውያንንም ርኵሰት ኮሞስን ተከተለ። 6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን አልተከተለውም። 7ያንጊዜም ሰሎሞን ለሞአብ ርኵሰት ለኮሞስ፥ ለአሞን ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም አንጻር በአለው ተራራ ላይ መስገጃን ሠራ። 8ሰሎሞንም ልዩ ከሆኑ ከአሕዝብ ለአገባቸው ሚስቶቹ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ ለጣዖቶቻቸውም መሥዋዕትን ሠዋ፤ ዕጣንም አጠነ።
9ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡናውን መልሶአልና እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ቍጣን ተቈጣ። 10ስለዚህም ነገር ወደ ባዕድ አምልኮት እንዳይሄድ፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ሁሉ ይጠብቅና ያደርግ ዘንድ አዘዘው፤ ልቡናው ግን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልሆነም። 11እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው፥ “ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ትእዛዜንና ሕጌን አልጠብቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ከፍዬ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። 12ነገር ግን ከልጅህ እጅ እከፍለዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። 13ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ሀገሬ ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልከፍልም።”
14እግዚአብሔርም ኤዶማዊው አዴርን ከረምማቴር ወገን የኤልያዳሔ ልጅ ኤስሮምን የሲባ ንጉሥ ጌታውን አድረዓዛርን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣ። ሰዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። የዓመፁም አበጋዝ እርሱ ነበር። ደማስቆንም እጅ አደረጋት። በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ በእስራኤል ላይ ጠላት ሆነ። ኤዶማዊው አዴርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር ነበር።
በሰሎሞን ላይ ጠላት እንደ ተነሣበት
15ዳዊትም ኤዶምያስን ባጠፋ ጊዜ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ ተወግተው የሞቱትን ሊቀብር በወጣ ጊዜ፥ የኤዶምያስንም ወንድ ሁሉ በገደለ ጊዜ፥ 16ኢዮአብና እስራኤልም ሁሉ የኤዶምያስን ወንድ ሁሉ እስኪገድሉ ድረስ ስድስት ወር በዚያ ተቀምጠው ነበር። 17አዴር፥ ከእርሱም ጋር ከኤዶምያስ ሰዎች የሆኑ የአባቱ አገልጋዮች ሁሉ ኰበለሉ፤ ወደ ግብፅም ገቡ። አዴር ግን ገና ሕፃን ነበር። 18ከምድያምም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ ከእነርሱም ጋር ከፋራን ሰዎችን ወሰዱ፤ ወደ ግብፅም መጡ፤ ወደ ግብፅም ንጉሥ ወደ ፈርዖን ሄዱ፤ አዴርም ወደ ፈርዖን ገባ። እርሱም ቤት ሰጥቶ ቀለብ ዳረገው። 19አዴርም በፈርዖን ፊት እጅግ ባለምዋል ሆነ። የሚስቱንም የቴቄምናስን ታላቅ እኅት ሚስት አጋባው። 20የቴቄምናስ እኅት ወንድ ልጅ ጌንባትን ለአዴር ወለደችለት፤ ቴቄምናስም በፈርዖን ልጆች መካከል አሳደገችው፤ ጌንባትም በፈርዖን ልጆች መካከል ነበረ። 21አዴርም በግብፅ ሳለ ዳዊት እንደ አባቶቹ እንዳንቀላፋ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ አዴር ፈርዖንን፥ “ወደ ሀገሬ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ” አለው። 22ፈርዖንም፥ “እነሆ፥ ከእኔ ዘንድ ወደ ሀገርህ መሄድ የፈለግህ ምን አጥተህ ነው?” አለው። አዴርም፥ “አንዳች አላጣሁም፤ ነገር ግን ልሂድ” ብሎ መለሰ። አዴርም ወደ ሀገሩ ተመለሰ።
23እግዚአብሔርም ደግሞ ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር የኰበለለውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ጠላት አድርጎ አስነሣበት። 24ዳዊትም የሲባን ሰዎች በገደለ ጊዜ ሬዞን ሰዎችን ሰብስቦ የጭፍራ አለቃ ሆነ፤ ወደ ደማስቆም ሄዱ፥ በዚያም ተቀመጡ፤ በደማስቆም ላይ አነገሡት። 25በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረ። አዴርም ያደረጋት ክፋት ይህች ናት፤ እስራኤልን አስጨነቀ በኤዶምያስም ነገሠ።
ኢዮርብዓም እንደሚነግሥ ትንቢት እንደ ተነገረለት
26ከሳሪራ ሀገር የሆነ የኤፍሬማዊው የናባጥና ሳሩሃ የተባለች የመበለት ልጅ ኢዮርብዓም የሰሎሞን አገልጋይ ነበረ። 27እርሱም ያደረገው ይህ ነው በንጉሡ በሰሎሞን ላይ እጁን አነሣ፤ ሰሎሞንም በዳርቻ ያለ ቅጥርንና የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጥር ሠርቶ ጨረሰ። 28ኢዮርብዓምም ጽኑዕ ኀያል ሰው ነበረ፤ ሰሎሞንም ጐልማሳው ኢዮርብዓም በሥራ የጸና መሆኑን ባየ ጊዜ በዮሴፍ ነገድ ሥራ ሁሉ ላይ ሾመው። 29ከዚህ በኋላም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ ከመንገድም ገለል አደረገው፤ አኪያም አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር። ሁለቱም በሜዳ ነበሩ። 30አኪያም የለበሰውን አዲስ ልብስ ይዞ ከዐሥራ ሁለት ቀደደው። 31ኢዮርብዓምንም አለው፥ “ዐሥር ቅዳጅ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እለያታለሁ፤ ዐሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ። 32ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ሀገሮች ሁሉ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን ሁለት ነገድ ይቀሩለታል፤ 33ትቶኛልና፥ ለሲዶናውያንም ርኵሰት ለአስጠራጢስ፥ ለሞአብም አምላክ ለኮሞስ፥ ለአሞንም ልጆች አምላክ ለሞሎክ ሰግዶአልና፥ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ በፊቴ ቅን ነገርን ያደርግ ዘንድ በመንገዶቼ አልሄደምና። 34መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ። 35መንግሥቱንም ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። 36ስሜንም ባኖርሁባት በዚያች በመረጥኋት ከተማ በኢየሩሳሌም ለባሪያዬ ለዳዊት በፊቴ ሁልጊዜ መብራት ይሆንለት ዘንድ ለልጁ ሁለት ነገድን እሰጠዋለሁ። 37አንተንም እወስድሃለሁ፤ ነፍስህም በወደደችው ሁሉ ላይ አነግሥሃለሁ፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ። 38ባሪያዬም ዳዊት እንዳደረገ፥ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትሰማ፥ በመንገዴም ብትሄድ፥ በፊቴም የቀናውን ብታደርግ፥ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ብትጠብቅ፥ ከአንተ ጋር እኖራለሁ፤ ለዳዊትም እንደ ሠራሁለት የታመነ ቤትን እሠራልሃለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጥሃለሁ። 39ስለዚህም የዳዊትን ዘር አስጨንቃለሁ፤ ነገር ግን በዘመን ሁሉ አይደለም።” 40ሰሎሞንም ኢዮርብዓምን ሊገድለው ወደደ፤ ኢዮርብዓምም ተነሥቶ ወደ ግብፅ ሀገር፥ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሱስቀም ኰብልሎ ሄደ፥ ሰሎሞንም እስኪሞት ድረስ በግብፅ ተቀመጠ።
የሰሎሞን ሞትና የሮብዐም መንገሥ
(2ዜ.መ. 9፥29-31)
41የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ ጥበቡም ሁሉ፥ እነሆ፥ በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 42ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። 43ሰሎሞንም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 11: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in