YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ፊልሞና 1

1
ሰላምታ
1ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ከሆነው ጳውሎስና ከወንድሙ ጢሞቴዎስ፥ ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥ 2#ቈላ. 4፥17።ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነው ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን፤
3ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የፊልሞና ፍቅርና እምነት
4በጸሎቴ እያሰብኩህ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ። 5በጌታ በኢየሱስ ዘንድ፤ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለው ፍቅርህና እምነትህ እሰማለሁና። 6የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ 7የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ! በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና።
ጳውሎስ ስለ ኦኔሲሞስ ያቀረበው ምልጃ
8ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ 9ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። 10#ቈላ. 4፥9።በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ ኦኔሲሞስ እለምንሃለሁ፤ 11በፊት አልጠቀመህም ነበር፤ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም በጣም እየጠቀመን ነው። 12እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደምትቀበል አድርገህ ተቀበለው። 13እኔስ ስለ ወንጌል በገጠመኝ እስራት አንተን ወክሎ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው በፈቅድኩ ነበር፤ 14ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም ነገር ላደርግ አልፈልግሁም።
15ዳግመኛ ተቀብለህ ለዘለዓለም እንድትይዘው ይሆናል ምናልባት ለጊዜው የተለየህ፤ 16ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባርያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም ሆነ በጌታ ዘንድ ከባርያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? 17እንግዲህ እንደ ወንድምህ እስከ ቆጠርከኝ ድረስ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። 18በአንዳች ነገር በድሎህ እንደሆነ ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቁጠር፤ 19እኔ ጳውሎስ “እኔ እመልሰዋለሁ፤” ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አላስታውስህም። 20አዎን፥ ወንድሜ ሆይ! በጌታ ይህንን ጉዳይ ፈጽምልኝ። በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ።
21ከምጠይቅህ ይልቅ አብልጠህ እንደምታደርግ በማወቅ እንደምትታዘዝም በመተማመን እጽፍልሃለሁ። 22ደግሞ ከዚህም ጋር የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ፤ በጸሎታችሁ ለእናንተ እንደምሰጥ ተስፋ አደርጋለሁና።
የመጨረሻ ሰላምታ
23 # ቈላ. 1፥7፤ 4፥12። በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኔ ጋር የታሰረ ኤጳፍራ 24#የሐዋ. 12፥12፤25፤ 13፥13፤ 15፥37-39፤ ቈላ. 4፥10፤ የሐዋ. 19፥29፤ 27፥2፤ ቈላ. 4፥10፤ ቈላ. 4፥14፤ 2ጢሞ. 4፥10፤ ቈላ. 4፥14፤ 2ጢሞ. 4፥11።አብረውኝም የሚሠሩ ማርቆስና አርስጥሮኮስ ዴማስም ሉቃስም ሰላምታ ያቀርቡልሃል።
25የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in