YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 40

40
1እግዚአብሔርም ቀጠለ፤ ኢዮብንም እንዲህ አለው፦
2“በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን የሚችል አምላክን መተቸት ይችላልን?
ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።”
3ኢዮብም መለሰ፤ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦
4“እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፥ የምመልስልህ ምንድነው?
እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።
5አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፥
ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።”
6ጌታም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
7“እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥
እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
8በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን?
አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ላይ ትፈርዳለህን?
9እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን?
ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጉዳለህን?
10ግርማንና ልዕልናን ተላበስ እንጂ፥
ሞገስንና ክብርን ተጐናጸፍ።
11የቁጣህን ሙላት አፍስስ፥
ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው።
12ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፥
በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው።
13በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፥
በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን።
14በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ልታድንህ እንደምትችል
እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ።
15አንተን እንደሠራሁ የሠራሁትን ጉማሬ#40፥15 ዕብራይስጡ “ብሄሞት” ይላል። ቃል በቃል አውሬ እንደማለት ነው።፥ እስኪ፥ ተመልከት፥
እንደ በሬ ሣር ይበላል።
16እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፥
ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው።
17ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፥
የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።
18አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፥
አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።
19እርሱ የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ አውራ ነው፥
ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው።
20የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ
ምግብን ያበቅልለታል።
21ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥
በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል።
22ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፥
የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል።
23እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፥
ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል።
24ዐይኖቹ እያዩ ይያዛልን?
አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?
25በውኑ አዞውን#40፥25 ዕብራይስጡ “ሌዊያታን” ይላል። በመንጠቆ ታወጣለህን?
ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን?
26ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን?
ወይስ በችንካር መንጋጋውን ትበሳለህን?
27በውኑ ወደ አንተ በእጅግ ይማጸናልን?
በለሰለሰ ቃል ይናገርሃልን?
28በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን?
ወይስ ለዘለዓለም ባርያ ታደርገዋለህን?
29ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን?
ወይስ ለሴት ልጆችህ መዝናኛ እንዲሆን ታስረዋለህን?
30አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን?
ወይስ ነጋዴዎች ያካፋፍሉታልን?
31በውኑ ቆዳውን በጦር፥
ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን?
32እስቲ እጅህን በላዩ ጫን፥
ፍልሚያውን በሚገባ ታስታውሳለህ፥ ሁለተኛም አይለምድህም።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in