YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 41

41
1 # መዝ. 73፥14፤ ኢሳ. 27፥1። “እነሆ፥ ተስፋ ማድረግ ከንቱ ነው፥
እርሱን ማየቱ ብቻ ያብረከርካል።
2ማንም ሊቀሰቅሰው የሚደፍር የለም፥
እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው?
3እመልስለትስ ዘንድ መጀመሪያ የሰጠኝ ማን ነው?
ከሰማይ ሁሉ በታች ያለው ገንዘቤ ነው።
4ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፥
ስለ መልካም ሰውነቱም ዝም አልልም።
5የውጪ ልብሱን ማን ይገፋል?
በጥንድ መንጋጋውስ ውስጥ ማን ይገባል?
6የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው?
በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ።
7የጀርባው ቆዳዎች ጠንካራ ናቸው፤ አቤት ኩራት!
በጥብቅ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው።
8እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና
ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም።
9እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፥
እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል።
10ሲያስነጥስ ብልጭታ ያወጣል፥
ዐይኖቹም እንደ ንጋት ወገግታ ናቸው።
11ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፥
የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል።
12እንደ ፈላ ድስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ
ከአንፍንጫው ጢስ ይወጣል።
13እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፥
ነበልባልም ከአፉ ይወጣል።
14አንገቱ በጣም ጠንካራ ነው፥
ግርማ በፊቱ ይዘፍናል።
15ሥጋውም እርስ በርስ የተጣበቀ ነው፥
ምንም ላያንቀሳቅሳቸው በእርሱ ላይ ጸንተዋል።
16ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፥
እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው።
17በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፥
ከድንጋጤም የተነሣ ይናወጣሉ።
18ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም።
19ብረትን እንደ ገለባ፥
ናስንም እንደ ነቀዝ እንጨት ይቆጥራል።
20ቀስት ሊያባርረው አይችልም፥
የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል።
21ዱላን እንደ ገለባ ይቈጥረዋል፥
ሰይፎች ሲንቀጠቀጡ ይስቃል።
22የአካሉ ታችኛው ክፍል እንደ ስለታም ገል ነው፥
እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል።
23ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፥
ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል።
24በስተ ኋላው ብሩህ መንገድን ያበራል፥
ቀላዩም ሽበት ይመስላል።
25ያለ ፍርሃት የተፈጠረ፥
እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም።
26ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፥
በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy