YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 42

42
1ኢዮብም መለሰ፤ ጌታንም እንዲህ አለው፦
2“ሁሉንም ማድረግ እንድምትችል፥
ሐሳብህም ሊከለከል ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ።
3 # ኢዮብ 38፥2። ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው?
ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥
የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ።
4 # ኢዮብ 38፥3። እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፥
እጠይቅህማለሁ፥ አንተም አሳውቀኝ።
5መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፥
አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፥
6ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፥
በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።”
7ጌታም ይህንን ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ፥ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፦ “እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። 8አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ አገልጋዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ጥፋታችሁ#42፥8 ቃል በቃል፦ “እንደ እብደታችሁ”። እንዳላደርግባችሁ ጸሎቱን እሰማለሁ፥ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።” 9ቴማናዊውም ኤልፋዝ ሹሐዊውም በልዳዶስ ናዕማታዊውም ሶፋር ሄደው ጌታ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ ጌታም የኢዮብን ጸሎት ሰማ።
10 # ኢዮብ 1፥1-3። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ሲጸልይ ጌታ ምርኮውን መለሰለት፥ ጌታ ቀድሞ በነበረው ፋንታ በሁለት እጥፍ አሳድጎ ለኢዮብ ሰጠው። 11ወንድሞቹና እኅቶቹ ቀድሞም ያውቁት የነበሩት ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፥ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በሉ፥ ስለ እርሱም አዘኑለት፥ ጌታም ካመጣበት ክፉ ነገር ሁሉ አጽናኑት፥ እያንዳንዳቸውም ብርና የወርቅ ቀለበት ሰጡት። 12ጌታም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፥ ዐሥራ አራት ሺህም በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት። 13ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሆኑለት። 14የመጀመሪያይቱንም ይሚማ፥ ሁለተኛይቱንም ቃስያ፥ ሦስተኛይቱንም ቄሬንህፉክ#42፥14 በግሪኩ ትርጒም “አማልቶያስ ቂራስ” ይላል። ብሎ ሰየማቸው። 15እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆችም ያሉ የተዋቡ ሴቶች በአገሩ ሁሉ አልተገኙም፥ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። 16ከዚህም በኋላ ኢዮብ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፥ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። 17ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy