YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 11

11
የሊስያስ የመጀመሪያው ጦርነት (ዘመቻ)
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ የንጉሡ መምህርና ዘመድ የሆነው ሊስያስ የመንግሥት ጉዳይ ዋና ኃላፊ ስለሆነ በቅርቡ በተደረገው ነገር መታገሥ አቃተው፤ 2ከፈረሰኛ ጦሩ ጋር ሰማንያ ሺህ ያህል እግረኛ ጦረኞች ሰብስቦ አይሁዳውያንን ለመውጋት ይገሠግሥ ጀመር፤ ከተማዋን የግሪኮች መኖሪያ ሊያደርጋት አስቦ ነበር፤ 3ቤተ መቅደስን እንደ ሌሎቹ የአረማውያን ጣዖት ቤቶች ማስገበርና የሊቀ ካህናቱን ክብር በየዓመቱ እንዲሸጥ ማድረግ አስቦ ነበር፤ 4የእግዚአብሔርን ሥልጣን ከምንም አልተቆጠረም፤ በትዕቢት የተነፍቶ እምነቱን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እግረኞች ጦረኞቹ፥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፈረሰኞቹ፥ በሰማንያ ዝሆኖቹም ላይ ጥሎ ነበር።
5በይሁዳ አገር በደረሰ ጊዜ ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ከኢየሩሰሌም ርቃ ወደምትገኘው ምሽግ ወደ ቤተሱር ተጠጋና ከበባት፤ 6ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ሰዎች ሊስያስ ምሽጐቹን እንደከበበ አወቁ፤ እስራኤልን የማይድን ደግ መልአክ እንዲልክ ከሕዝቡ ጋር ሆነው እየተጨነቁና እንባቸውን እያፈሰሱ እግዚአብሔርን ለመኑት። 7ይሁዳ መቃቢስ ራሱ አስቀድሞ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንድሞቻቸውን ለማዳን ከእርሱ ጋር አደጋውን እንዲጋፈጡ ሌሎቹን መከረ፤ እነርሱም በጀግንነት ተነሣስተው አብረው ወጡ፤ 8ገና በኢየሩሳሌም አጠገብ እያሉ ወርቃዊ የጦር መሣሪያ የጨበጠ፤ ነጭ ልብስ የለበሰ ፈረሰኛ መሪአቸው ሆኖ አዩ፤ 9ሁለም በአንድ ላይ መሐሪውን እግዚአብሐርን አመሰገኑ፤ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ጨካኝ አውሬዎችንና የብረት ግንቦችን እንኳ ለመውጋት ብርታትን አገኙ። 10እግዚአብሔር ሰለራራላቸውና ከሰማይ ረዳት ስላገኙ ለውጊያ ተሰልፈው ገሠገሡ፤ 11እንደ አንበሶች ዘልለው ወደ ጠላት መሀል ገቡና ዐሥራ አንድ ሺህ እግረኛ ጦረኞችና አንድ ሺህ ስድስት መቶ ፈረሰኞችን ወግተው ጣሉ፤ የጠላት ጦር እንዲሸሽ አደረጉ። 12ከእነርሱ አብዛኞቹ ቆስለው መሣሪያዎቻቸውን እየጣሉ አመለጡ፤ ሊስያስም በሚያሳፍር ሁኔታ ሸሽቶ አመለጠ።
በአይሁዳውያንና በሊስያስ መካከል ሰላም ሆነ
ስምምነቱን የተመለከቱ አራቱ ዳብዳቤዎች
13ነገር ግን ሊስያስ ነገሩን ልብ አድርጐ ተመለከተና የደረሰበትን መሸነፍ አሰበ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ረዳታቸው በመሆኑ ዕብራውያን የማይሸነፉ መሆናቸው ስለገባው መልእተኞች ወደ እነርሱ ላከ፤ 14በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ለመስማማት ሐሳብ አቀረበ፤ ንጉሡም ወዳጃችሁ እንዲሆን አስረዳዋለሁ ሲል ተስፋ ሰጣቸው። 15ይሁዳ መቃቢስ ለሁሉም ጥቅም መሆኑን አስባ ሊስያስ ያቀረበለት ሐሳብ ተቀበለ፤ ይሁዳ መቃቢስም ስለ አይሁዳውያን ጉዳይ በጽሑፍ ለሊስያስ ያቀረበውን ነገር ሁሉ ንጉሡ እሺ ብሎ ተቀበለ።
16ሊስያሰ ለአይሁዳውያን የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፥ “ሊስያስ ለአይሁዳውያን ሁሉ ሰላምታ ያቀርባል። 17እናንተ የላካችኋቸው ዮሐንስና አቤሴሎም የጻፋችሁትን አቅርበውልን የጻፉትን ነገሮች እንድቀበል ጠይቀውኛል። 18በእኔ በኩል የሚቻለውን ሁሉ ከተቀበልሁ በኋላ ለንጉሡ ማቅረብ የሚገባውን ለንጉሡ አቅርቤአለሁ፤ (እርሱም ተቀብሏል) 19እናንተ ለመንግሥት መልካም አሳቢዎች ናችሁ ከተገኛችሁ እኔም ለእናንተ ወደ ፊት መልካም ነገር አደርጋለሁ። 20ስለ ዝረዝሩ መልእክተኞቻችሁና የእኔም ሰዎች ከእናንተ ጋር እንዲነጋገሩ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። 21ደኀና ሁኑ፤ በ 148 ዓመት በ 24 የዲዮ ስቆሪንቶስ ወር”። (አዳር ከ 26 የካቲት እስከ 27 መጋቢት ያለው ወር ነው።) 22የንጉሡ ደብዳቤም እንዲህ ይል ነበር፤ “ንጉሥ አንጥዮኩስ ለወንድሙ ለሊስያስ ሰላምታ ያቀርባል፤
23“አባታችን ወደ አማልክት ሄዷል (ሞቷል)፤ እኛም የመንግሥታችን ሰዎች ሁሉ የውስጥ ጉዳያቸውን እየፈጸሙ ያለ ችግር እንዲኖሩ እንፈልጋለን፤ 24አይሁዳውያን አባታችን የፈለገውን የግሪካውያን ልማድ መከተል እንደማይወዱ ሰምተናል፤ የራሳቸውን ልዩ መንገድ ይመርጣሉ፤ ሕጋቸውን ለመጠበቅ እንዲፈቀድላቸውም ይፈልጋሉ፤ 25ስለዚህ ይህ ሕዝብም ከችግር ነጻ እንዲሆን በመመኘት ቤተ መቅደሳቸው እንዲመለስላቸውና በአባቶቻቸው ልማድ መሠረት ዜጐች ሆነው እንዲኖሩ ወስነናል። 26አንተ ወደ እነርሱ ሰው ብትልክና የሰላም እጅህን ብትዘረጋላቸው መልካም ነው፤ በዚህ ዓይነት እኛ የተከተልነውን መንገድ አውቀው እምነት ይኖራቸዋል፤ በመልካመ ሁኔታም ሥራቸውን ያከናውናሉ”። 27ወደ አይሁዳውያን የተላከው የንጉሡ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤
ንጉሡ አንጥዮኩስ ለአይሁዳውየን ምክር ቤትና ለሌሎችም አይሁዳውያን ሰላምታ ያቀርባል
28“ደኀና እንድትሆኑ ምኞታችን ነው፤ እኛ በመልካም ጤና ላይ እንገኛለን፤ 29መነላዎስ እናንተ ወደ ሀገራችሁ ተመልሳችሁ ጉዳያችሁን እንድትፈጽሙ መፈለጋችሁን ነግሮናል፤
30“ከ 30 ጻንጢቆ (የካቲት-መጋቢት) በፊት ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ሁሉ የሰላም እጃችንን እንደምንሰጣቸው እናረጋግጣለን። 31አይሁዳውያን እንደ ቀድሞው ጊዜ ሕጋቸውን መከተልና ልዩ ምግባቸውን መመገብ ይችላሉ፤ ከእነርሱ ማንም ባለማወቅ በሚያደርገው ስሕተት በምንም ዓይነት አይጠይቅም። 32ከእናንተ ጋር ተነጋግሮ የሚያረጋግጥላችሁን መነላዎስን ልኬላችኋለሁ። ደኀና ሁኑ”።
33በ 148 ዓመት በ 15 በጻንጢቆ ወር (የካቲት-መጋቢት) 34ሮማውያንም በበኩላቸው ለአይሁዳውያን እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈዋል። “ኩዋንቶስ መማዮስ፥ ቲቶ ማንሊዮስ፥ ማኒዮስ ሰርጅዮስ፥ ሮማውያን መልእክተኞች ለአይሁድ ሕዝብ ሰላምታ ያቀርባሉ፤
35“የንጉሡ ዘመድ ሊስያስ የፈቀደላችሁን ሁሉ እኛም ፈቅደናል። 36ነገር ግን ለንጉሡ አቀርባቸዋለሁ ስላላቸው ነገሮች ከመረመራቸው በኋላ በቶሎ ወደ እኛ ሰው ላኩና እኛ ወደ አንጾኪያ ከመሄዳችን በፊት ለእናንተ በሚጠቅማችሁ ዓይነት ነገሮቹን ለንጉሡ እንድንገልጽለት ይሁን። 37ሐሳባችሁ ምን መሆኑን እኛም እንድናውቅ ቶሎ ብላችሁ ሰው ላኩብን። 38ደኀና ሁኑ።” በ 148 ዓመት በጻንጢቆ ወር በ 15 ተፃፈ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in