YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 10

10
የቤተ መቅደስ መንጻት
1ይሁዳ መቃቢስ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ እግዚአብሔር እየመራው ቤተ መቅደሱንና ከተማዋን እንደገና አስተካከለ፤ 2የውጭ አገር ሰዎች ለሕዝቡ ያቋቋሙዋቸውን መሠዊያዎችና የአምልኮ ቦታዎች አፈራረሱ። 3ቤተ መቅደሱ ካነጸ በኋላ ሌላ መሠዊያ ሠሩ፤ ከድንጋይ አዲስ እሳት አውጥተው ሁለት ዓመት ከተቋረጠ በኋላ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ዕጣን አጨሱ፤ ፋኖሶቹን አበሩ፤ የተቀደሱትን ዳቦዎች አወጡ። 4እነዚህን ሥርዓቶች ከፈጸሙ በኋላ በግምባራቸው ተደፍተው፤ እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት መቅሰፍት ላይ እንዳይጥላቸው፥ ኃጢአት ላይ ቢወድቁም በመጠኑ እንዲያርማቸው (እንዲቀጣቸው) እንጂ ከተሳዳቢዎችና ከጨካኞች አረማውያን እጅ እንዳይጥላቸው ለመኑት። 5ይህ የቤተ መቅደስ መንጻት የሆነው ልክ ባዕዳን ቤተ መቅደሱን ባረከሱበት ቀን በ 25 በሴከሎ ወር ነው። 6ስምንቱን ቀን ልክ እንደ ዳስ በዓል በደስታ አከበሩ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይህን በዓል ያከበሩት እንደ ዱር አራዊት በተራራና በዋሻዎች ውስጥ ሆነው እንደ ነበር አስታወሱ። 7ስለዚህ የዛፍ ቅርንጫፎችና ቅጠል ዘንባባም ይዘው ቅዱሱን ቦታ እንዲያነጹ ያበቃቸውን አምላክ በዘማሬ አመሰገኑ። 8በድምፅ ብልጫ ወስነው እነዚህን ቀኖች የአይሁድ ሕዝብ በየዓመቱ እንዲያከብሯቸው አዘዙ።
ይሁዳ ከጎረቤቶቹ ሕዝቦች እንዲሁም ከአንጥዮኩስ
5ኛ ሹም ከሊሲያስ ጋር የደረገው ትግል የአንጥዮኩስ ግዛት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት 9እንግዲህ የአንጥዮኩስ ኤጲፋኔስ ሞት በእንደዚህ ሁኔታ ተፈጸመ፤ 10አሁን በአንጥዮኩስ ኤውጶጥሮስ ጊዜ የሆነውን እንተርካለን። እርሱ የዚያ የክፉ ሰው ልጅ ነው፤ በጦርነት ሳቢያ የደረሰበትን ጭንቀት እንናገራልን። 11መንግሥቱን ከወረሰ በኋላ እርሱ የቀለሲርያና የፊኒቆስ ገዥ የነበረውን ሊስያስን የጉዳዩ አለቃ አድርጐ ሾመው። 12ማቅሮን የተባለው ጰጠሎማዮስ ግን በአይሁዳውያን ላይ በተደረገው በደል ፍትሕ እንዲያገኙ ያደረገ፥ በሰላም ለማሰተዳደር የሞከረ የመጀመሪያው ሰው እርሱ ነበር። 13በዚህ ጉዳይ የንጉሡ ወዳጆች በኔውጳጥሮስ ላይ ከሰውት ፊሎመትሮስ አደራ የሰጠውን ቆጵሮስን ስለተወና ወደ አንጥዮኩስ ኤጲፋኔስጐን ስለዞረ የዘወትር ከሐዳ ተብሎ ተጠራ። በሠራውም ክብሩን ጠብቆ ስላልተገኘ መርዝ ጠጥቶ ሞተ። ጐርጊያስ እና የአዱማያውያን የመከለከያ ግንብ 14ጐርጊያስ የሀገሩ የጦር መሪ ሆኖ ቅጥረኞች ወታደሮችን ያስተዳድር ነበር፤ ከአይሁዳውያን ጋር ጦርነት ለመግጠም ሁልጊዜ አጋጣሚ ነገር ይፈልግ ነበር። 15በዚያኑ ጊዜ በደንብ የተዘጋጁትን ምሽጐች ይዘው የነበሩ ኤዱማውያን ይሁዳውያንን ያስቸግሩ ነበር፤ ከኢየሩሳሌም ሸፍተው የሄዱትን ሰዎች ተቀብለው ጦርነትን ያነሣሡ ነበር። 16ነገር ግን ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ወታደሮች በግብጽ ጸሎት ካደረጉና እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዲሆን ከለመኑ በኋላ ወደ ኤዱማውያን ምሽጐች መገሥገሥ ጀመሩ። 17በጥንካሬ ተዋግተው ባታዎችን ያዙባቸው፤ በግንቡ ላይ ሆነው ይዋጉ የነበሩትን ሁሉ አስወገዷቸው፤ ሊቃወሙዋቸው የመጡትንም ገደሉዋቸው፤ ከሃያ ሺህ የማያንሱ ሞቱ። 18ዘጠኝ ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ለውጊያ የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ባላቸው በተለይ ጠንካራ በሆኑ ሁለት ግንቦች ውስጥ መሽገው ነበር፤ 19ይሁዳ መቃቢስ ስምዖንንና ዮሴፍን፥ ዘኬዎስንም ከሰዎቹ ጋር ብዙዎችን እዚያ እንዲከብቡዋቸው አድርጐ እርሱ ራሱ በጣም አስፈላጊ ወደሆኑ ቦታዎች ሄደ። 20ነገር ግን ለገንዘብ የተሰገበገቡትን የስምዖንን ሰዎች፥ ግንቦቹን የሚጠብቁ ሰዎች በገንዘብ አታለሏቸው፤ ሰባ ሺህ ድርሀም ተቀብለው እንዳንዶቹ እንዳያመልጡ አድርገዋል። 21ይህን ነገር ለይሁዳ መቃቢስ በነገሩት ጊዜ የጦር አለቆቹን ሰብስቦ ጠላቶቻቸውን በእነርሱ ላይ በመለቀቅ ወንድሞቻቸውን ለገንዘብ ሲሉ ሸጠዋል ብሎ ጥፋተኞቹን ከሰሳቸው፤ 22ስለዚህ እንደ ከሐዲዎች ተቆጥረው እንዲገደሉ አደረገና ሁለቱን ግንቦች ያዘ። 23በሱ የሚመራውን ጦር በመልካም መርቶ በእነዚህ በሁለት ምሽጐች የነበሩትን ከሃያ ሺህ በላይ የሚሆኑትን ሰዎች ደመሰሰ። ይሁዳ ጢሞቴዎስን አሸንፎ ጋዜርን ያዘ 24በፊት ጊዜ አይሁዳውያን አሸንፈውት የነበረ ጢሞቴዎስ ብዙ የውጭ አገር ሰዎች አሰልፎ፥ ከእስያ የመጡ ብዙ ፈረሶች ሰብስቦ፥ በጦር መሣሪያ ሰዎቹን ለማንበርከክ አስቦ ወደ ይሁዳ ምድር መጣ። 25ጦሩ በተቃረበ ጊዜ ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ሰዎች በራሳቸው ላይ አፈር ነሰነሱና በወገባቸው የተለተለ ልብስ አሸረጡ። 26እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸውና በኦሪት ቃል መሠረት የጠላቶቻቸው ጠላት እንዲሆንላቸው የተቃዋሚዎቻቸው ተቃዋሚ እንዲሆን ይለምኑት ጀመር። 27ከዚህ ጸሎት በኋላ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ከከተማው በጣም ርቀው ገሠገሡ፤ ከጠላት አጠገብ በደረሱ ጊዜ ቆሙ። 28በጠዋት የፀሐይ ብርሃን በታየ ጊዜ በዚህም በዚያም ውጊያውን ጀመሩ፤ ግማሾቹ በእግዚአብሔር ተማጥነው በጀግንነታቸው እንደሚቀናቸውና ድል እንደሚነሱ ዋስትና ኖሯቸው፥ ሌሎቹ ቁጣቸውን የውጊያው መሪ አድርገው ይዋጉ ነበር። 29ጦርነቱ እጅግ በተጋጋለም ጊዜ የወርቅ ልጓም ባላቸው ፈረሶች ላይ የተቀመጡ አይሁዳውያንን የሚመሩ አምስት መልከ መልካም ሰዎች ከሰማይ ለጠላቶች ታዩ። 30ይሁዳ መቃቢስን በመካከላቸው አድርገው በጋሻቸው እየተከላከሉለት እንዳይነካ ይጠብቁት ነበር፤ በጠላቶች ላይ ግን ቀስትና መብረቅ ይወረውሩ ነበር፤ በዚህ ዓይነት ጠላቶች ተደናግጠውና ዐይኖቻቸውን ታውረው ወዲያና ወዲህ ተበታተኑ። 31ሃያ ሺህ አምስት መቶ የእግረኛ ጦር ወታደሮችና ስድስት መቶ ፈረሰኞች ተገደሉ። 32ጢሞቴዎስም ቀርአስ ወደሚያዝባት በብርቱ ወደምትጠበቀው ጋዜር ወደምትባለው ምሽግ ሄደ። 33ግን ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ሰዎች ደስ እያላቸው አራት ቀን ከበው አስጨነቋት፤ 34በውስጧ የሚገኙ ሰዎች በቦታው አለመደፈር ተማምነው ብዙ ይሳደቡ ነበር፤ መጥፎ ቃላትም በመናገር አልተቆጠቡመ ነበር። 35አምስተኛው ቀን በሆነ ጊዜ የአይሁድ መቃቢስ ሃያ ወጣት ወታደሮች በስድባቸው በጣም ተናደው፥ በወንድነት ጀግንነትና በታላቅ ቁጣ ተነሣሥተው ወደ ታላቁ ግንብ እየዘለሉ ወጡና እዚያ ያገኟቸውን ሁሉ ገደሉ። 36ሌሎችም በዚሁ ዓይነት በግንቡ ውስጥ ወደነበሩት ሰዎች በሌላ በኩል ገብተው ግንቦቹን አቃጠሉ፤ እሳት አንድደውም ተሳዳቢዎቹን በሕይወታቸው እያሉ አቃጠሉዋቸው። የፊተኞቹ ወታደሮች መዝጊያዎቹን ሰባበሩና የቀረውን ጦር ሠራዊት አስገቡ፤ ከተማዋን ለመያዝም የመጀመሪያዎቹ ሆኑ። 37በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ የነበረውንም ጢሞቴዎስን ገደሉት፤ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ቀሪያንና አጶሎፋንንም ገደሉ። 38ይህንን ካደረጉ በኋላ በእስራኤል ብዙ መልካም ነገር ያደረገላቸውንና ድልን የሰጣቸውን አምላክ በዝማሬና በውዳሴ አመሰገኑት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in