YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 14

14
የስምዖን ምስጋና
1በመቶ ሳባ ሁለት (144) ዓ.ዓ ንጉሥ ዲመትሪዮስ ሠራዊቱን ሰብስቦ ትሪፎንን ለመውጋት እርዳታ ፍለጋ ወደ ሜዶን ሄደ። 2ዲመትሪዮስ ወደ እርሱ አገር መግባቱን ሰምቶ የፋርስና የሜዶን ንጉሥ አርሴቅስ ዲመትሪዮስን በሕይወቱ ይዞ እንዲያመጣው ከጦር መሪዎቹ አንዱን ላከ፤ 3ይህ የጦር መሪ ሄደና የዲመትሪዮስን ሠራዊት ወግቶ አሸነፈ፤ ዲመትሪዮስን ማርኮ ወደ አርስቄስ አመጣው፤ አርስቄስም እስር ቤት አስገባው፤ 4ስምዖን በነበረበት ጊዜ ሁሉ የይሁዳ ምድር እረፍት አገኘች፤ እርሱ የሕዝቡን ደኀንነት ይፈልግ ነበር፤ እርሱ በነረበረት ጊዜ ሁሉ ሰዎች በሥልጣኑና በክብሩ ተደሰቱ፤ 5ኢዮጴን በመያዝ በክብር ላይ ክብርን ጨመረ፤ ኢዮጴን ወደቡና ወደ ማዴትራኒያን ባሕር መሄጃ በር አደረጋት፤ 6የሀገሪቷን ድንበሮች አስፋፋ፥ በሚገባም መራት፤ 7ብዙ ምርኮኞችን አሰፈረ፤ ጌዘርን፥ ቤተሱርን፥ ምሽጉንም ያዘ፤ እርኩስ ነገርን ሁሉ ነቅሎ አጠፋ፤ ማንም ሊቋቋመው አልቻለም። 8ሰዎች ምድራቸውን በሰላም ያርሱ ነበር፤ ምድር ፍሬዋን ትሰጥ ነበር፤ በሜዳው ላይ የበቀሉ ዛፎችም ፍሬአቸውን ይለግሱ ነበር። 9ሽማግሌዎች በአደባባዮች ተቀምጠው ስለብልጽግና ብቻ ይናገሩ ነበር፤ ጐልማሶች የክብርና የጦር ልብስ ይለብሱ ነበር። 10ለከተሞች ምግብ አቀረበላቸው፤ የተጠናከሩ ምሽጐች አበጀላቸው፤ በዚህ ዓይነት ዝናው እስከ ምድር ዳርቻዎች ድረስ ተሰማ። 11በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምን አደረገ፤ እስራኤልም ታላቅ ደስታን አገኘች። 12እያንዳንዱ ሰው በወይኑና በበለሱ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የሚያስፈራቸው ማንም አልነበረም። 13ከምድራቸው ሊወጋቸው የሚችል ጠላት አልነበረም፤ ነገሠታቱ ሁሉ ተደምስሰዋል። 14የተጐሳቆሉትንም ሰዎች አበረታታ፤ ተንኮለኞችንና ከሐዲዎችንም ረገጣቸው። 15ሕጉን ለማስከበር በብርቱ ጣረ፤ ቤተ መቅደስን አዲስ ክብር አለበሳት፤ በበርካታ የተቀደሱ ቁሰቁሶችም አበለጸጋት።
ከእስፖርታና ከሮም የነበረው ግንኙነት መታደስ
16በሮምና በእስፖርታ የዮናታን ሞት ተሰማና ትልቅ ኀዘን ሆነ። 17ነገር ግን ወንድሙ ስምዖን በእርሱ ምትክ ሊቀ ካህናት መሆኑና የሀገሪቱና የከተሞች ገዥ መሆኑንም ባወቁ ጊዜ 18ከወንድሞቹ ከይሁዳና ከዮናታን ጋር የተዋዋሉትን ውል በነሃስ ሰሌዳ ላይ ጽፈው ላኩለት። 19ሕዝቡ በተሰበሰበበት በኢየሩሳሌም ተነበበ። 20እስፖርታውያን የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ እንዲህ ይላል፥ “ሹማምንትና የእስፖርታ ከተማ ለወንድሞቻቸው ለሊቀ ካህናት ሰምዖንና ለሽማግሌዎች፥ ለካህናት ለአይሁድ ሕዝብ ሁሉ ሰላምታ ያቀርባሉ። 21ወደ ሕዝባችን የተላኩት መልክተኞች ብልጽግናችሁንና ክብራችሁን ነግረውናል፤ በመምጣታቸውም ተደስተናል። 22እነርሱ የገለጹልንን በሕዝቡ ውሳኔዎች መካከል እንዲህ ስንል ጽፈነዋል፤ የአንጥዮኩስ ልጅ ኑመንዮስና የኢያሶን ልጅ አንጢጰጥሮስ የአይሁድ መልእክተኞች ሆነው ከእኛ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማደስ ወደ እኛ መጥተዋል፤ 23ሕዝቡ ደስ ብሎት እነዚህን ሰዎች በክብር ተቀብለቸዋል፤ የንግግራቸውንም ግልባጭ በሕዝቡ መዝገብ ውስጥ አኑሮታል፤ ይህም የተደረገው የእስፖርታ ሕዝብ እያስታወሰሰው እንዲኖር ነው። እንዲሁም ግልባጩ ለሊቀ ካህናት ስምዖን ተጽፎል”። 24ከዚህ በኋላ ስምዖን ከሮማውያን ጋር ያለውን ቃል ኪዳን ለማጽናት አንድ ሺህ ምናን ከሚመዝን ከትልቅ የወርቅ ጋሻ ጋር አመንዮስን ወደ ሮም ላከው።
ስለ ስምዖን ንብረት የወጣ አዋጅ
25ሕዝቡ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ለስምዖንና ለልጆቹ ምን ውለታ ነው የምንመልሰው? 26ምክንያቱም እርሱና ወንድሞቹ፤ የአባቱም ቤት ሁሉ ጠንካሮች ሆነው ተገኝተዋል፤ በጦር መሣሪያ የእስራኤልን ጠላቶች አጥፍተዋል፤ ለሕዝቡ ነጻነትን አስገኝተዋል”። ስለዚህም ይህንን ክቡር ተግባር በብረት (በነሐስ) ሰሌዳ ላይ ጽፈው፤ በሐውልት ላይ አድርገው በጽዮን ተራራ ላይ አቆሙት፤ 27የጽሑፍ ግልባጭ የሚለው እንዲህ ነው፤ “ኤሉስ በገባ በዓሥራ ስምንት መቶ ሰባ ሁለት (መስከረም 13 ቀን 140 ዓመተ ዓለም) የሊቀ ካህናቱ ስምዖን ሦስተኛ ዓመት ነበር። 28ያንጊዜ በአሳራማኤል፥ በካህናቱና በሕዝቡ፥ በሀገሪቱ ሹማምንትና ሽማግሌዎች በተደረገው ታላቅ ጉባኤ እንዲህ ሲሉ ለእኛ ለእስራኤላውያን አስታውቀውናል። 29በሀገሪቱ ላይ በደረሱት የማያባሩ በርካታ ጦርነቶች የኢዮአሪብ ልጆች ዘር የሆነው የማታትያስ ልጅ ስምዖን እና ወንድሞቹ ለአደጋ ተጋልጠዋል፤ ቤተ መቅደሳቸውንና ሕግም ተከብረው እንዲኖሩ በማለት የሕዝባቸውን ጠላቶች ተቋቁመዋል፤ ሕዝባቸውንም ታላቅ ክብር አጐናጽፈዋል።” 30ዮናታን የእርሱን ሕዝብ ሰብስቦ የእነርሱ ሊቀ ካህናት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም በዕረፍቱ ከቀደሙትና ካለፉት አባቶቹ ጋር ተቀላቀለ። 31ይህን የሰሙ የአይሁድ ጠላቶች አገራቸውን ለመውረርና ለማጥፋት፤ እጃቸውንም በቤተ መቅደሳቸው ላይ ለማንሣት ፈለጉ፤ 32በዚያን ጊዜ ስምዖን ተነሥቶ ስለ ሕዝቡ ተዋጋ፤ ከገንዘቡም ብዙ ወጪ አድርጐ የብሔራዊ ጦር ሰዎችን አስታወቀ፤ ደሞዛቸውንም ከፈለ። 33የይሁዳን ከተሞችና በቀድሞ ጊዜ በድንበር ላይ የጠላት ኃይል የነበረውን ቤተሱራን አጠናከረ፤ ከአይሁዳውያን ተዋጊዎች እዚያ አደረገ። 34በባሕር ኢዮጴን በፊት ጠላቶች ይኖሩባት የነበረችው ጌዘሮን በአዞጥ ድንበር አጠናከረ፤ አይሁዳውያንን አደረገበት፤ የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ እዚያ አስቀመጠላቸው። 35ሕዝቡ የስምዖን ታማኝነትና ለራሱ ሕዝብ ሊሰጥ ያሰበውን ክብር ተመለከተለት፤ ባደረገው ሁሉ፥ ለሕዝቡ ባሳየው እውነተኛነትና እምነት ምክንያት የእነርሱ መሪና ሊቀ ካህናት እንዲሆን አደረገጉት፤ ምክንያቱም የእርሱ የዘወትር ጥረቱ ሕዝቡን ከፍ ለማድረግ ነበረ። 36ስምዖን በዘመኑ አረማውያንና በዳዊት ከተማ በኢየሩሳሊም የነበሩትን ሰዎች ከሀገሪቱ ነቅሎ ለመጣል ችሏል፤ እነርሱም እዚያ ምሽጋቸውን አድርገው ነበር፤ ከዚያ እየወጡ የቤተ መቅደሱን ዙሪያ ያረክሱ ነበር፤ ለቅድስናው የማይስማማ ነገር ለማድረግ በብርቱ ይጥሩ ነበር። 37እርሱ በዚህ ቦታ ላይ የአይሁድ ወታደሮች አደረገና ለሀገሪቱና ለከተማይቱ ጥበቃ አጠናከረው፤ የኢየሩሳሌምን መካበቢያዎች ከፍ አድርጐ ሠራ። 38ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዲሜጥሮስ ሊቀ ካህንነቱን አጸናለት፤ 39ከወዳጆቹ ቍጥር ውስጥ አገባው፤ ክብርም አቀዳጀው። 40ሮማውያን አይሁዳውያንን እንደ ወዳጆቻቸው፥ እንደ የጦር ጓደኞቻቸውና እንደ ወንድሞቻቸው የሚያዩዋቸው መሆኑን ተገንዝቦ ነበር፤ 41አይሁዳውያንና ካህናት አንድ ታማኝ ነቢይ እስኪነሣላቸው ድረስ ስምዖንን ለዘወትር መሪና ሊቀ ካህናት አድርገው መሾማቸውን ሰምቶ ነበር። 42የጦር መሪና የቤተ መቅደስ ኃላፊ ሆኖ መመረጡን፥ የሥራ መሪዎችንና የሀገር አስተዳዳሪዎችን፥ የጦር መሣሪያና የምሽጐች ኃለፊዎችን ለመሾም መመረጡንም አውቋል፤ 43የተቀደሱ ነገሮች ኃላፊ ነው፤ ሁሉም ሊታዘዙለት ይገባል፤ የሀገሪቱ ጽሑፎች ሁሉ በስሙ እንዲጻፉ ያደርጋል፤ የከፋይና የወርቅ ልብስ እንዲለብስ ይፈቀድለታል። 44ከሕዝቡም ሆነ ከካህናት መካከል ማንም እርሱ የደነገገውን ማፈረስ አይገባውም፤ የእርሱን ትእዛዝ መቃወም ወይም ያለ እርሱ ፈቃድ በሀገሪቱ ውስጥ ስበስባ ማድረግ ከፋይ መልበስ ወይም የወርቅ መቆለፊያ ማድረግ ማንም አይገባውም። 45የእርሱን ሕግጋት የሚያፈርስ ሁሉ ቅጣት ይገባዋል። 46ሕዝቡ በሙሉ እነዚህን መብቶች ለስምዖን ለመስጠት ተስማማ። 47ስምዖንም እሺ ብሎ የሊቀ ካህነቱን ሥራና የጦር መሪነቱን፤ የአይሁዳውያንና የካህናት ሹም መሆንን፥ የሁሉ በላይ ራስ መሆንን ተቀበለ። 48ይህ ቃል በብረት (በነሐስ) ሰሌዳ ላይ እንዲጻፍና በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ በሚታይ ቦታ እንዲቀመጥ ወሰኑ። 49ለስምዖንና ለልጆቹ የሚያገለግሉ የእነዚሁ ግልባጭም በግምጃ ቤት እንዲቀመጡ ተስማሙ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in