YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 71

71
የእግዚአብሔርን ጥበቃ መማጸን
1እግዚአብሔር ሆይ! እንድትጠብቀኝ ወደ አንተ ስለ መጣሁ
ኀፍረት እንዲደርስብኝ አታድርግ!
2በጽድቅህ ከችግር እንዳመልጥ አድርገህ አውጣኝ
አድምጠህም አድነኝ።
3በምሄድበት ቦታ ሁልጊዜ አንተ ኀያል አምባዬ ሁን፤
አንተ ኀያል አምባዬና ምሽጌ ስለ ሆንክ በትእዛዝህ አድነኝ።
4አምላኬ ሆይ! ከክፉ ኀይልና
ርኅራኄ ከሌለው ዐመፀኛ እጅ አድነኝ።
5ጌታ እግዚአብሔር ሆይ!
ተስፋዬን በአንተ ላይ አደርጋለሁ፤
ከልጅነቴ ጀምሮ መታመኛዬ አንተ ነህ።
6በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በአንተ ላይ እታመናለሁ፤
ከእናቴ ማሕፀን እንድወለድ ያደረግኸኝ አንተ ነህ፤
እኔም ዘወትር አመሰግንሃለሁ።
7አንተ ብርቱ ተከላካይ ስለ ሆንክልኝ
ሕይወቴ ለብዙዎች ምሳሌ ሆኖአል።
8አንደበቴ በአንተ ምስጋና የተሞላ ነው፤
ስለ ክብርህም ቀኑን ሙሉ እናገራለሁ።
ድምፄንም ከፍ አድርጌ ለአንተ ምስጋና አቀርባለሁ።
9አሁንም በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤
ደካማ በምሆንበትም ጊዜ አትተወኝ።
10ጠላቶቼ በእኔ ላይ ክፉ ነገር ይመክራሉ፤
ሊገድሉኝ የሚፈልጉትም በእኔ ላይ ያሤራሉ።
11“እግዚአብሔር ትቶታል፤ ተከታትለን እንያዘው፤
የሚያድነው ማንም የለም” ይላሉ።
12አምላክ ሆይ! ከእኔ አትራቅ፤
አምላክ ሆይ! ፈጥነህ እርዳኝ።
13ተቃዋሚዎቼ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤
ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ይናቁ፤ ይዋረዱም።
14እኔ ግን ዘወትር አንተን ተስፋ አደርጋለሁ፤
በበለጠም መላልሼ አመሰግንሃለሁ።
15ምንም እንኳ ማስተዋል ቢያዳግተኝ፥
አንደበቴ ስለ ትክክለኛ ፍርድህና
ስለ አዳኝነትህ ቀኑን ሙሉ ይናገራል።
16ጌታ እግዚአብሔር ሆይ!
መጥቼ ኀያል ሥራዎችህን ዐውጃለሁ፤
ትክክለኛ ፍርድ የመስጠት ኀይል የአንተ ብቻ መሆኑን እናገራለሁ፤
17አምላክ ሆይ! አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርከኝ፤
ገና አሁንም ድንቅ ሥራህን እናገራለሁ።
18አምላክ ሆይ! ሥልጣንህን ለሚመጣው ትውልድ፥
ኀይልህንም ለሚመጡት ሁሉ እስክገልጥና
አርጅቼ እስክሸብት ድረስ እንኳ አትተወኝ።
19አምላክ ሆይ! ጽድቅህ እስከ ሰማይ ይደርሳል፤
ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤ አምላክ ሆይ! አንተን የሚመስል ማን ነው?
20በብዙ ችግርና መከራ እንድሠቃይ አድርገኸኛል፤
ሆኖም እንደገና ከመሬቱ ጥልቅ ጒድጓድ አውጥተህ
አዲስ ሕይወትን ትሰጠኛለህ።
21ክብሬን ታሳድጋለህ፤
እንደገናም ታጽናናኛለህ።
22አምላኬ፥ የእስራኤል ቅዱስ ሆይ!
ስለ ታማኝነትህ በበገና አመሰግንሃለሁ፤
በመሰንቆም የምስጋና መዝሙር አቀርብልሃለሁ።
23ያዳንከኝ እኔ የምስጋና መዝሙር ስዘምርልህ።
ከንፈሮቼ የደስታ ጩኸት ይጮኻሉ።
24ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ስላፈሩና ግራ ስለ ተጋቡ
አንደበቴ ቀኑን ሙሉ ስለ እውነተኛ ርዳታህ ይናገራል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ መዝሙር 71