መጽሐፈ መዝሙር 55
55
ወዳጁ የከዳው ሰው ጸሎት
1አምላክ ሆይ! ጸሎቴን ስማ፤
ልመናዬንም ቸል አትበል!
2የልቤ ጭንቀት ሰላም ስላልሰጠኝ
እባክህ፥ አድምጠህ መልስ ስጠኝ።
3ከጠላቶቼ ዛቻ የተነሣ ፈርቼአለሁ፤
በክፉዎችም ጭቈና ደቅቄአለሁ፤
እነርሱ መከራን ያመጡብኛል፤
በቊጣና በጥላቻ ይመለከቱኛል።
4ልቤ በውስጤ አስጨንቆኛል፤
የሞት ፍርሀትም ወደቀብኝ።
5ፍርሀትና ድንጋጤ ይዞኛል፤
መላ ሰውነቴም ተሸብሮአል።
6እንደ ርግብ ክንፎች ቢኖሩኝ
ዕረፍት ወደማገኝበት ስፍራ
በርሬ መሄድን በወደድኩ ነበር።
7ወደ ሩቅ ስፍራ ተጒዤ
መኖሪያዬን በበረሓ ባደረግሁ ነበር።
8ከዚህ ከደረሰብኝ ዐውሎ ነፋስና ሞገድ
መጠለያ ስፍራ ለማግኘት ፈጥኜ በሄድኩ ነበር።
9እግዚአብሔር ሆይ!
በከተማይቱ ውስጥ ዐመፅንና ብጥብጥን ስላየሁ፥
የክፉዎችን ምክር አጥፋ፤ ዕቅዳቸውንም ደምስስ!
10ችግርና ጥፋት የሞላባት ነች።
ክፉዎችም ቀንና ሌሊት በቅጽሮችዋ ይዞራሉ።
11በከተማዋ ውስጥ ጥፋት አለ፤
አደባባዮችዋም በጭቈናና በአታላይነት የተሞሉ ናቸው።
12የሚሰድበኝ ጠላት አይደለም፤
ጠላት ቢሆንማ ኖሮ በታገሥኩ ነበር።
የሚታበይብኝም ባለጋራ አይደለም፤
ባለጋራ ቢሆንማ ኖሮ ከፊቱ በተሰወርኩ ነበር።
13ይህን ሁሉ የምታደርግብኝ አንተ ግን
ከእኔ ከራሴ የማልለይህ፥ ጓደኛዬ፥ የቅርብ ወዳጄ ነህ።
14በቤተ መቅደስ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አብረን ስንሄድ
በመልካም ንግግሮች እንደሰት ነበር።
15ልባቸው የክፋት ማደሪያ ስለ ሆነ
በጠላቶቼ ላይ ድንገተኛ ሞት ይምጣባቸው!
በሕይወት ሳሉ ወደ ሙታን ዓለም ይውረዱ!
16እኔ ግን ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤
እርሱም ያድነኛል።
17ዘወትር ጠዋት፥ እኩለ ቀንና ማታ፥
ችግሬንና ሐዘኔን ለእርሱ አስታውቃለሁ፤
እርሱም ድምፄን ይሰማል።
18እጅግ ከበዙ ጠላቶቼ ጋር
ከማደርገው ጦርነት በሰላም ይመልሰኛል።
19እነርሱ ስለማይለወጡና አምላክን ስለማይፈሩ
ለዘለዓለም በዙፋኑ ላይ ያለው አምላክ
የእኔን ጸሎት ሰምቶ ያዋርዳቸዋል።
20ጓደኛዬ ወዳጆቹን አጠቃቸው፤
ቃል ኪዳኑንም አፈረሰ።
21ንግግሩ እንደ ቅቤ የለዘበ ነው፤
በልቡ የሚያስበው ግን ጦርነትን ነበር
አንደበቱ ከዘይት ይበልጥ የለሰለሰ ነው፤
ነገር ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ነው።
22ችግርህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤
እርሱም በእንክብካቤ ይጠብቅሃል፤
እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን
ከቶ ለችግር አሳልፎ አይሰጣቸውም።
23አምላክ ሆይ! አንተ ግን ክፉዎችን ወደ ጥልቅ ጒድጓድ ትጥላቸዋለህ፤
እነዚያ ነፍሰ ገዳዮችና ከዳተኞች
ግማሽ ዕድሜአቸውን እንኳ አይኖሩም፤
እኔ ግን በአንተ እተማመናለሁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 55: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997