YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 10

10
ትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ!
ስለምን እንደዚህ ርቀህ ትቆማለህ?
በችግር ጊዜስ ስለምን ትሰወራለህ?
2ክፉ ሰዎች ይታበያሉ፤ ድኾችንም ያሳድዳሉ፤
ለሌሎች በዘረጉት ወጥመድ ራሳቸው ይጠመዱ።
3ኃጢአተኛ በክፉ ምኞቱ ይመካል፤
ጌታ ሆይ! እነዚህ ስግብግብ ሰዎች
ይጠሉሃል፤ ይሰድቡህማል።
4ክፉዎች ስለ እግዚአብሔር ግድ የላቸውም
በትዕቢታቸውም እግዚአብሔር የለም ብለው ያስባሉ።
5ክፉ ሰው በሁሉ ነገር ይሳካለታል፤
የእግዚአብሔርን ፍርድ ግን ሊረዳ አይችልም፤
በጠላቶቹም ላይ ይሳለቃል።
6በሐሳቡ “የሚያነቃንቀኝ የለም፤
ምንም ችግር ሳያጋጥመኝ ሁልጊዜ እደሰታለሁ” ይላል።
7ንግግሩም በእርግማን፥ በሐሰትና በዛቻ የተሞላ ነው፤
ተንኰልና ክፉ ነገር በአንደበቱ ናቸው። #ሮም 3፥14።
8በመንደሮች አጠገብ ይሸምቃል፤
ረዳት የሌላቸውን ደካሞች ይጠባበቃል፤
ንጹሑን ሰው በድብቅ ይገድላል።
9እርሱም እንደ አንበሳ ተደብቆ ይቈያል፤
ድኾችን ለመያዝ ይሸምቃል፤
እነርሱንም በአሽክላው ይዞ ይጐትታቸዋል።
10እርሱ መትቶ ይጥላቸዋል፤
ረዳት የሌላቸው ደካሞች ምስኪኖችም የእርሱ ሰለባ ሆነው ይወድቃሉ።
11ኃጢአተኛ በሐሳቡ፦
“እግዚአብሔር ረስቶአል፤
ፊቱንም ሸፍኖ በፍጹም አያይም!” ይላል።
12እግዚአብሔር ሆይ፥ ተነሥ! አምላክ ሆይ፥ ኀያል ክንድህን አንሣ!
የተጨቈኑትንም ችላ አትበላቸው።
13ክፉ ሰዎች ለምን አያከብሩህም?
ለምንስ በልባቸው “እግዚአብሔር አይቀጣንም” ይላሉ?
14አምላክ ሆይ! አንተ ግን ችግርንና ጭንቀትን አይተህ
ልታስወግዳቸው መፍትሔ ታዘጋጃለህ፤
ችግረኛ ራሱን ለአንተ ይሰጣል፤
አንተም የሙት ልጆችን ትረዳለህ።
15የኃጢአተኞችንና የክፉ ሰዎችን ኀይል አድክም፤
ከእንግዲህ ወዲያ ክፋትን እንዳያደርጉ
በክፉ ሥራቸው ሁሉ ቅጣቸው።
16እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፤
ለሌሎች አማልክት የሚሰግዱ ሕዝቦች ግን
ከምድሩ ይጠፋሉ።
17እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምስኪኖችን ጸሎት ትሰማለህ፤
ልመናቸውንም አድምጠህ ታበረታታቸዋለህ።
18በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር
ሌሎችን ለማስፈራራት እንዳይችል፥
አንተ ለወላጅ አልባና ለተጨቈኑ ሰዎች
ትከላከላለህ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in