YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 8

8
ኢየሱስ አራት ሺህ ሰዎችን መመገቡ
(ማቴ. 15፥32-39)
1በዚያን ሰሞን እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም፤ ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ 2“እነዚህ ሰዎች እነሆ፥ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ቈይተዋል፤ ምንም የሚበሉት ምግብ ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤ 3እንዲሁ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይደክማሉ፤ እንዲያውም ከእነርሱ አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ናቸው።”
4ደቀ መዛሙርቱም፦ “ታዲያ፥ በዚህ በረሓ ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚበቃ እንጀራ ማግኘት ማን ይችላል?” ሲሉ መለሱለት። 5ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤
እነርሱም “ሰባት እንጀራ አለን፤” አሉት።
6እርሱም በመሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ይዞ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አቀረቡ። 7ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎችም ነበሩአቸው፤ ስለ ዓሣዎቹም እግዚአብሔርን ካመሰገነ በኋላ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። 8ሰዎቹም ሁሉ በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቊርስራሽ ሰብስበው ሰባት ትላልቅ መሶብ ሙሉ አነሡ። 9የተመገቡት ሰዎች አራት ሺህ ያኽል ነበሩ፤ ኢየሱስ እነርሱን አሰናበታቸው። 10ከዚያ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሆኖ ወደ ዳልማኑታ አውራጃ ሄደ።
ተአምራት ለማየት የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 16፥1-4)
11ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጡና ከእርሱ ጋር መከራከር ጀመሩ፤ ሊፈትኑትም አስበው ከሰማይ አንድ ተአምር እንዲያሳያቸው ጠየቁት። #ማቴ. 12፥38፤ ሉቃ. 11፥16። 12ኢየሱስ በመንፈሱ በመቃተት፦ “የዚህ ዘመን ትውልድ ተአምር እንዲደረግለት ስለምን ይፈልጋል? በእውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ተአምር አይደረግለትም!” አላቸው። #12፥39፤ ሉቃ. 11፥29። 13ትቶአቸውም እንደገና በጀልባ ሆኖ ወደ ማዶ ተሻገረ።
የፈሪሳውያንና የሄሮድስ እርሾ
(ማቴ. 16፥5-12)
14ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ በጀልባው ውስጥ ከአንድ እንጀራ በቀር ምንም አልነበራቸውም። 15ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠንቀቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። #ሉቃ. 12፥1።
16እነርሱም “ይህን ማለቱ፥ ምናልባት እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
17ኢየሱስም ይህንኑ ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እንጀራ ስለሌለን ነው ብላችሁ ስለምን ታስባላችሁ? ገና ምንም የማታስተውሉና የማይገባችሁ ናችሁን? ልባችሁስ ገና እንደ ደነዘዘ ነውን? 18ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮስ እያላችሁ አትሰሙምን? እንዴትስ ትዝ አይላችሁም? #ኤር. 5፥21፤ ሕዝ. 12፥2፤ ማር. 4፥12። 19ለመሆኑ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?”
እነርሱም “ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ” አሉት።
20“እንዲሁም ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም “ሰባት መሶብ ሙሉ” አሉት።
21እርሱም “ታዲያ፥ ገና አታስተውሉምን?” አላቸው።
ኢየሱስ በቤተ ሳይዳ አንድ ዐይነ ስውር መፈወሱ
22ወደ ቤተ ሳይዳም በደረሱ ጊዜ ሰዎች አንዱን ዕውር ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እንዲዳስሰውም ለመኑት። 23እርሱም ማየት የተሳነውን ሰው እጅ ይዞ እየመራ ከመንደር ወደ ውጪ አወጣው፤ በሰውየውም ዐይኖች ላይ ምራቁን እንትፍ ብሎ እጁን ጫነበትና “አንዳች ነገር ታያለህን?” ሲል ጠየቀው።
24ዐይነ ስውሩም ቀና ብሎ፥ “አዎ ሰዎች ይታዩኛል፤ ግን እንደሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ፤” አለ።
25እንደገናም ኢየሱስ በሰውየው ዐይኖች ላይ እጁን ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው ትኲር ብሎ አየ፤ ድኖም ሁሉን ነገር አጥርቶ ማየት ጀመረ። 26ከዚያም በኋላ ኢየሱስ “ወደ መንደሩ አትግባ፤” ብሎ ወደ ቤቱ እንዲሄድ አሰናበተው።#8፥26 የግዕዝ ሐዲስ ኪዳን፥ በ 1947 ዓ.ም. የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስና በአንዳንድ የጥንት የግሪክ የብራና ጽሑፎች የሚከተለውን ይጨምራሉ፦ “በዚያም ይህን ለማንም አትንገር።”
ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ጴጥሮስ መግለጡ
(ማቴ. 16፥13-20ሉቃ. 9፥18-21)
27ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የፊልጶስ ቂሳርያ በሚባለው ክፍለ ሀገር አካባቢ ወዳሉት መንደሮች አመሩ፤ በመንገድም ላይ ሳሉ ኢየሱስ፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው።
28እነርሱም፦ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ ሌሎች ኤልያስ ነው፤ ሌሎችም ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል፤” ሲሉ መለሱለት። #ማር. 6፥14-15፤ ሉቃ. 9፥7-8።
29“እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ “አንተ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። #ዮሐ. 6፥68-69።
30ኢየሱስም፦ “ስለ እኔ ለማንም እንዳትናገሩ፤” ብሎ አስጠነቀቃቸው።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 16፥21-28ሉቃ. 9፥22-27)
31ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል ማስተማር ጀመረ፤ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።” 32ይህን ነገር በግልጥ ነገራቸው፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ገለል አድርጎት ይገሥጸው ጀመር። “እንዲህ አትበል” ሲል ተቈጣው። 33ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና ጴጥሮስን፦ “አንተ ሰይጣን ከእኔ ኋላ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብም!” ሲል ገሠጸው።
ክርስቶስን መከተል የሚጠይቀው መሥዋዕትነት
(ማቴ. 10፥38-3916፥24-28ሉቃ. 9፥23-2714፥25-27)
34ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ #ማቴ. 10፥38፤ ሉቃ. 14፥27። 35ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል፤ #ማቴ. 10፥39፤ ሉቃ. 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25። 36ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? 37ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል? 38በዚህ በከሐዲና በኃጢአተኛ ትውልድ ፊት በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ እኔም የሰው ልጅ በአባቴ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር ስመጣ በእርሱ አፍርበታለሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in