YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 9

9
የኢየሱስ መልክ መለወጥ
(ማቴ. 17፥1-13ሉቃ. 9፥28-36)
1ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ አሁን እዚህ ካሉት መካከል አንዳንዶች የእግዚአብሔር መንግሥት በታላቅ ኀይል ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አሉ፤” አላቸው።
2ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ ወደ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ፤ በፊታቸውም መልኩ ተለወጠ። #2ጴጥ. 1፥17-18። 3ልብሱ እጅግ አንጸባረቀ፤ በዓለም ላይ ማንም አጣቢ ያን ያኽል ሊያነጣ እስከማይችል ድረስ ነጭ ሆነ። 4በዚያን ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ተገልጠው ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። 5ጴጥሮስም ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! እዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። 6ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እጅግ ደንግጠው ስለ ነበር ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር።
7ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፦ “የምወደው ልጄ ይህ ነው! እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ ተሰማ #ማቴ. 3፥17፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22። 8ወዲያውም ዞር ብለው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።
9ከተራራውም ሲወርዱ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል አዘዛቸው።
10ቃሉንም ሰምተው በልባቸው ያዙት፤ ይሁን እንጂ “ይህ ከሞት መነሣት ምን ማለት ይሆን?” እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 11እነርሱም፦ “የሕግ መምህራን መጀመሪያ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ስለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። #ሚል. 4፥5፤ ማቴ. 11፥14።
12እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ይሁን እንጂ፥ የሰው ልጅ ከባድ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚናቅ የተጻፈው እንዴት ነው? 13እኔ ግን ኤልያስ ቀደም ብሎ መጥቶአል፤ ሰዎችም ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል” እላችኋለሁ።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ልጅ መፈወሱ
(ማቴ. 17፥14-21ሉቃ. 9፥37-43)
14ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው በመጡ ጊዜ ብዙ ሰዎች በዙሪያቸው ተሰብስበው አዩ፤ የሕግ መምህራንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይከራከሩ ነበር። 15ሕዝቡም ሁሉ ኢየሱስን ባዩት ጊዜ በመገረም ተደናገጡ፤ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። 16ኢየሱስም “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት በምን ጉዳይ ነበር?” ሲል ጠየቃቸው።
17ከሕዝቡም መካከል አንዱ፥ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መምህር ሆይ፥ ድዳ በሚያደርግ መንፈስ የተያዘውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ 18በሚነሣበትም ጊዜ ይጥለዋል፤ አፉም ዐረፋ እየደፈቀ ጥርሶቹን ያፋጫል፤ ሰውነቱም ደርቆ እንደ በድን ይሆናል፤ ርኩሱንም መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።”
19ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታምኑ ሰዎች! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” 20እነርሱም ልጁን ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩሱም መንፈስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ ወዲያው ልጁን ጥሎ አንፈራገጠው፤ ልጁም በመሬት ላይ እየተንከባለለ ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። 21ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያኽል ጊዜ ነው?” ሲል ጠየቀው።
አባትየውም እንዲህ አለ፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው። 22ሊገድለውም እየፈለገ ብዙ ጊዜ በእሳትና በውሃ ውስጥ ይጥለዋል፤ ግን አንዳች ነገር ማድረግ ብትችል እባክህ እዘንልን! እርዳንም!”
23ኢየሱስም “ብትችል” ትላለህን? “ለሚያምን ሰው ሁሉ ነገር ይቻላል!” አለው።
24ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “ማመንስ አምናለሁ፤ ግን ማመን በሚያቅተኝ ነገር ሁሉ ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ።
25ኢየሱስም ሕዝቡ እየተራወጡ ሲመጡ አየ፤ ርኩሱንም መንፈስ “አንተ ድዳና ደንቆሮ መንፈስ ከልጁ እንድትወጣ ወደ እርሱም ተመልሰህ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ብሎ ገሠጸው።
26ርኩሱም መንፈስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ልጁንም በጣም ካንፈራገጠው በኋላ ወጣ፤ ልጁም ልክ እንደ በድን በመሆኑ ብዙዎቹ የሞተ መሰላቸው። 27ኢየሱስ ግን የልጁን እጅ ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ።
28ኢየሱስም ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ለመሆኑ ይህን ርኩስ መንፈስ እኛ ልናስወጣው ስለምን አልቻልንም?” ብለው ለብቻው ጠየቁት።
29እርሱም “እንዲህ ዐይነቱ በጸሎትና [በጾም] ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም አይወጣም።” ሲል መለሰላቸው።
ኢየሱስ ስለ መሞቱና ስለ መነሣቱ ለሁለተኛ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 17፥22-23ሉቃ. 9፥43-45)
30ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያንን ስፍራ ትተው በገሊላ በኩል ሄዱ፤ ያለበትን ቦታም ማንም ሰው እንዲያውቅ ኢየሱስ አልፈለገም፤ 31ይህም የሆነው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከተገደለ በኋላ ግን በሦስተኛው ቀን ይነሣል።” እያለ ያስተምራቸው ስለ ነበር ነው።
32ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህ ነገር አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።
ከሁሉም የሚበልጥ ማን ነው?
(ማቴ. 18፥1-5ሉቃ. 9፥46-48)
33ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም መጡ፤ ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፦ “በመንገድ ሳላችሁ የተከራከራችሁበት ነገር ምን ነበር?” ሲል ጠየቃቸው።
34እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ይህም በመንገድ ሳሉ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ ይከራከሩ ስለ ነበረ ነው። #ሉቃ. 22፥24። 35እርሱም ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፥ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ማናቸውም ሰው የሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት፤” አላቸው። #ማቴ. 20፥26-27፤ 23፥11፤ ማር. 10፥43-44፤ ሉቃ. 22፥26። 36አንድ ሕፃን አምጥቶ በመካከላቸው አቆመው፤ ዐቅፎትም እንዲህ አላቸው፦ 37“እንደዚህ ካሉት ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ እኔን ሳይሆን፥ የላከኝን ይቀበላል።” #ማቴ. 10፥40፤ ሉቃ. 10፥16፤ ዮሐ. 13፥20።
የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው
(ሉቃ. 9፥49-50)
38ዮሐንስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያስወጣ አየን፤ ግን ከእኛም ጋር ስላልሆነ ከለከልነው፤” አለው።
39ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “በስሜ ተአምር እያደረገ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ የሚናገር ስለሌለ ተዉት፤ አትከልክሉት፤ 40እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነው፤ #ማቴ. 12፥30፤ ሉቃ. 11፥23። 41በእውነት እላችኋለሁ፤ የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ አንድ ብርጭቆ ውሃ እንኳ የሚያጠጣቸው ዋጋውን አያጣም፤” አላቸው። #ማቴ. 10፥42።
ለሰው መሰናክል ከመሆን መጠንቀቅ
(ማቴ. 18፥6-9ሉቃ. 17፥1-2)
42“ማንም ሰው በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትንንሾቹ አንዱን ከሚያስት ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። 43ስለዚህ እጅህ ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ ቈርጠህ ጣለው! ሁለት እጅ እያለህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ ጒንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። #ማቴ. 5፥30። 44ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱ የማይጠፋበት ስፍራ ነው። #9፥44 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 44 ይጨምራሉ፤ ቃሉም በቊ 48 ያለውን ይመስላል። 45እግርህም ቢያስትህ፥ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እግር እያለህ፥ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ፥ አንካሳ ሆነህ፥ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። [ 46ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱ የማይጠፋበት ስፍራ ነው።] #9፥46 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 46 ይጨምራሉ ቃሉም በቊ. 48 ያለውን ይመስላል። 47ዐይንህም ቢያስትህ፥ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን እያለህ፥ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። #ማቴ. 5፥29። 48ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱም የማይጠፋበት ስፍራ ነው። #ኢሳ. 66፥24።
49“መሥዋዕት በጨው እንደሚጠራ እያንዳንዱ ሰው በእሳት መጥራት አለበት። #9፥49 ስለ ጨውና ስለ እሳት ማጥራት ጉዳይ፦ ዘሌ. 2፥13፤ ሚል. 3፥2-3፤ ፊልጵ. 3፥17 ይመለከቷል።
50“ጨው መልካም ነው፤ ይሁን እንጂ፥ የጨውነቱን ጣዕም ካጣ በምን ታጣፍጡታላችሁ? #ማቴ. 5፥13፤ ሉቃ. 14፥34-35።
“በእናንተም የፍቅር ጨው ጣዕም ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ በሰላም ኑሩ፤” አለ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in