YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 15

15
ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰዱ
(ማቴ. 27፥1-211-14ሉቃ. 23፥1-5ዮሐ. 18፥28-38)
1ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሸንጎውም አባሎች ሁሉ ጋር ተማከሩ፤ ከዚያም በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። 2ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው፤” አለው።
3የካህናት አለቆች ግን ኢየሱስን በብዙ ይወነጅሉት ነበር። 4ስለዚህ ጲላጦስ “በስንት ነገር እንደሚከሱህ ተመልከት! ከቶ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል እንደገና ጠየቀው።
5ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ አሁንም ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠም።
ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት
(ማቴ. 27፥15-26ሉቃ. 23፥13-25ዮሐ. 18፥39-4019፥1-16)
6ጲላጦስ በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሰዎቹ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ይለቅላቸው ነበር። 7በዚያን ጊዜ በመንግሥት ላይ ተነሣሥተው፥ ሰው በመግደል ወህኒ ቤት የገቡ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከነዚህም ዐመፀኞች አንዱ በርባን የሚባለው ሰው ነበር። 8ሕዝቡም ወደ ጲላጦስ ቀርበው የተለመደውን ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠየቁት። 9እርሱም “የአይሁድን ንጉሥ ፈትቼ እንድለቅላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። 10ይህንንም ያለው የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ስለ ነበር ነው።
11የካህናት አለቆች ግን፥ “በእርሱ ፈንታ በርባን ይፈታልን፤” ብለው ጲላጦስን እንዲጠይቁ ሰዎቹን አነሣሡ። 12ጲላጦስም፦ “ታዲያ፥ ይህን የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላድርገው?” ሲል ሰዎቹን እንደገና ጠየቀ።
13እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ እንደገና ጮኹ።
14ጲላጦስም “ለምን? ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው።
እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ አብዝተው ጮኹ።
15ጲላጦስ ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን አስገረፈውና እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።
ወታደሮች በኢየሱስ ማፌዛቸው
(ማቴ. 27፥27-31ዮሐ. 19፥2-3)
16ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ የቀሩትንም ወታደሮች ሁሉ ጠሩ፤ 17ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበትና፤ 18“የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ በማፌዝ እጅ ይነሡት ነበር። 19በመቃ ራስ ራሱን ይመቱት ነበር፤ ምራቃቸውንም እንትፍ ይሉበት ነበር፤ በፊቱም በማላገጥ እየተንበረከኩ ይሰግዱለት ነበር። 20ካፌዙበትም በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው፥ የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።
የኢየሱስ መሰቀል
(ማቴ. 27፥32-44ሉቃ. 23፥26-43ዮሐ. 19፥17-27)
21ሲሄዱም ሳሉ የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። #ሮም 16፥13። 22ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ትርጒሙ የራስ ቅል ወደ ሆነው ስፍራ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። 23እዚያም ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም። 24ከዚህም በኋላ ሰቀሉት፤ ልብሶቹንም ማን ምን እንደሚወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት። #መዝ. 22፥18። 25ኢየሱስን ሲሰቅሉት ጊዜው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። 26ወንጀሉንም ለማመልከት “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር። 27ከኢየሱስም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አምጥተው አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። [ 28በዚህም ሁኔታ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤” የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጸመ።] #ኢሳ. 53፥12። #15፥28 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 28 ይጨምራሉ፦ ቃሉም በሉቃ. 22፥37 ያለውን ይመስላል።
29በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች ራሳቸውን በንቀት እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር፦ “አዬ፥ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው! #መዝ. 22፥7፤ 109፥25፤ ማር. 14፥58፤ ዮሐ. 2፥19። 30እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!”
31በዚህ ዐይነት የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራንም እርስ በርሳቸው እንዲህ እየተባባሉ ይዘባበቱበት ነበር፦ “ሌሎችን አድኖአል፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! 32እርሱ መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንይና እንመንበት!”
እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር።
የኢየሱስ ሞት
(ማቴ. 27፥45-56ሉቃ. 23፥44-49ዮሐ. 19፥28-30)
33ከቀኑም ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 34ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። #መዝ. 22፥1።
35በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ የእርሱን ጩኸት ሰምተው “እነሆ! ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። 36ከእነርሱም አንዱ ሮጠና ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ፤ እንዲጠጣውም በመቃ ላይ አድርጎ ለኢየሱስ ሰጠውና “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደ ሆነ እንይ!” አለ። #መዝ. 69፥21። #15፥36 ሰፍነግ፦ እንደ ኳስ ክብ ሆኖ በባሕር ውስጥ የሚበቅል ብቋያ፥ ሁለንተናው ዐይን፥ ውሃ መጣጭ፥ የባሕር እንጒዳይ ዐይነ በጎ መሳይ ነው።
37ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱም ከሥጋው ተለየች።
38የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። #ዘፀ. 26፥31-33። 39በመስቀሉ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረ የመቶ አለቃ ኢየሱስ እንዴት ነፍሱ ከሥጋው እንደ ተለየች ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፤” አለ።
በጎልጎታ የነበሩ ሴቶች
(ማቴ. 27፥55-56ዮሐ. 19፥25-27)
40በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ፥ አንዳንድ ሴቶችም በዚያ ነበሩ። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፥ ሰሎሜም ይገኙ ነበር። 41እነርሱ ኢየሱስ በገሊላ በነበረበት ጊዜ፥ ይከተሉትና ያገለግሉት ነበር። እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ብዙ ሌሎች ሴቶች ነበሩ። #ሉቃ. 8፥2-3።
የኢየሱስ መቀበር
(ማቴ. 27፥57-61ሉቃ. 23፥50-56ዮሐ. 19፥38-42)
42ቀኑ መሽቶ ስለ ነበር የሰንበት ዋዜማና የዝግጅትም ጊዜ ሆነ፤ 43በዚያኑ ጊዜ የአይሁድ ሸንጎ አባል የነበረ ዮሴፍ የሚባል፥ የተከበረ የአርማትያስ ሰው መጣ። እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበር። በድፍረት ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ለመነ። 44ጲላጦስም “እንዴት እንዲህ በቶሎ ሞተ?” ብሎ ተደነቀ። የመቶ አለቃውንም አስጠርቶ፥ “በእርግጥ ከሞተ ቈይቶአልን?” ሲል ጠየቀው። 45የኢየሱስን መሞት ከመቶ አለቃው ከሰማ በኋላ አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት። 46ዮሴፍ አዲስ የከፈን ልብስ ገዛና የኢየሱስን አስከሬን ከመስቀል አውርዶ ገነዘው፤ ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው። ትልቅ ድንጋይም አንከባሎ መቃብሩን ዘጋ። 47መግደላዊት ማርያምና የዮሳ እናት ማርያም ኢየሱስን የት እንደ ቀበሩት ይመለከቱ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in