ትንቢተ ሚክያስ 3
3
ሚክያስ የእስራኤልን መሪዎች መገሠጹ
1ከዚህም በኋላ እንዲህ አልኳቸው፦ “የእስራኤል ሕዝብ ልጆች መሪዎችና የእስራኤል ሕዝብ ገዢዎች! አድምጡ! ትክክለኛ ፍርድን ማወቅ ይገባችሁ አልነበረምን? 2እናንተ ግን መልካሙን ጠልታችሁ ክፉውን ወደዳችሁ፤ ሕዝቤን በቊመናቸው ቆዳቸውን ገፈፋችሁ፤ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያችሁ፤ 3የሕዝቤን ቆዳ ገፋችሁ አጥንታቸውን ቈራርጣችሁ ለአፍላልና ለድስት እንደሚቈራረጥ ሥጋ አደረጋችኋቸው፤ ሥጋቸውንም በላችሁ። 4እናንተም ተጨንቃችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትጮኹበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን እርሱ አይመልስላችሁም፤ ክፉ ሥራ ስለ ሠራችሁ ልመናችሁ አይሰማም።”
5እግዚአብሔር ስለ ሐሰተኞች ነቢያት እንዲህ ይላል፦ “ጥቅም የሚያገኙበት ሲሆን ‘ሰላም ይወርድላችኋል’ እያሉ ይሰብካሉ፤ ጥቅም በማያገኙበት ጊዜ ‘ጦርነት ይመጣባችኋል’ እያሉ በማወጅ ሕዝቡን ያስታሉ፤ 6ስለዚህ ራእይ የማያዩበት ሌሊት ይመጣባቸዋል፤ የማይገለጥላቸውም ጨለማ ሆኖባቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ራእይ አያዩም፥ ትንቢትም አይናገሩም። 7‘ራእይ እናያለን፥ ትንቢት እንናገራለን’ የሚሉ ሁሉ ስለማይሳካላቸው ይዋረዳሉ፤ እግዚአብሔርም መልስ ስለማይሰጣቸው ከማፈራቸው የተነሣ ፊታቸውን በእጃቸው ሸፍነው ይሄዳሉ።”
8እኔን ግን እግዚአብሔር በመንፈሱና በኀይሉ ሞልቶኛል፤ የእስራኤል ሕዝብ በደላቸውና ኃጢአታቸው ምን እንደ ሆነ አስታውቃቸው ዘንድ በግልጽ ትክክለኛ ፍርድን ለመስጠት ብርታትን ሰጥቶኛል። 9እናንተ ፍትሕን የምትጸየፉና ትክክለኛውን ነገር ሁሉ የምታጣምሙ የያዕቆብ ልጆች መሪዎች፥ የእስራኤል ሕዝብ አለቆች ይህን ስሙ፤ 10እናንተ ደም በማፍሰስ ጽዮንን፥ በደል በመሥራት ኢየሩሳሌምን የምትገነቡ ናችሁ። 11የከተማይቱም ሹማምንት የሚፈርዱት በጉቦ ነው፤ ካህናቱ ያለ ዋጋ አያስተምሩም፤ ነቢያቱም ያለ ገንዘብ ትንቢት አይናገሩም፤ ይህም ሁሉ ሆኖ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለ ሆነ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይመጣብንም” በማለት በእግዚአብሔር ይመካሉ።
12ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ ማሳ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ ቤተ መቅደሱም የተሠራበት ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ይሆናል። #ኤር. 26፥18።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997