ትንቢተ ሚክያስ 4
4
ሰላም የሚሰፍንበት የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚመጣ
(ኢሳ. 2፥1-4)
1የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ፥
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ
ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤
ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤
የብዙ መንግሥታት ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
2ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፥
“ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ፥
ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤
ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤
እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤
እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።”
3እርሱ በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤
በቅርብና በሩቅ ባሉ ታላላቅ መንግሥታት መካከል
ያለውን አለመግባባት ያስወግዳል፤
ስለ ሆነም ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥
ጦራቸውንም ወደ ማጭድ ይለውጣሉ፤
መንግሥት በመንግሥት ላይ ጦርነት አያነሣም፤
ከዚያ በኋላም የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም። #ኢዩ. 3፥10።
4እያንዳንዱ ሰው በተከለው ወይንና በለስ ጥላ ሥር በሰላም ያርፋል።
የሚያስፈራውም ነገር አይኖርም፤
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።#ዘካ. 3፥10።
5አሕዛብ ሁሉ እያንዳንዳቸው ጣዖቶቻቸውን ያመልካሉ፤ እኛ ግን አምላካችንን እግዚአብሔርን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እናመልካለን።
የእስራኤል ሕዝብ ከስደት መመለስ
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያ ቀን አንካሶችንና እኔ ስለ ቀጣኋቸው ተሰደው መከራ የደረሰባቸውን ሕዝቤን እሰበስባለሁ። 7አንካሶች ተርፈው እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ተጥለው የነበሩትን ብርቱ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔም በጽዮን ተራራ ላይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በእነርሱ ላይ እነግሣለሁ።”
8አንቺ የጽዮን ተራራ የመንጋው መጠበቂያ ግንብ ሆይ! የተሰጠሽ ተስፋ ይፈጸማል፤ የቀድሞ ሉዐላዊነትሽ ኢየሩሳሌምም ዋና ከተማነቷ ይመለስልሻል። 9እንደዚህ ከፍ አድርገሽ የምትጮኺው፥ ምጥ እንደ ያዛት ሴት የምትጨነቂው ለምንድን ነው? ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ አማካሪዎችሽ ሁሉ ስለ ጠፉ ነውን? 10የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ምጥ እንደ ያዛት ሴት እየቃተታችሁ ተንፈራፈሩ፤ ከከተማ ተባራችሁ በሜዳ ላይ ትሰፍራላችሁ ወደ ባቢሎንም ትሄዳላችሁ፤ ይሁን እንጂ በዚያ እግዚአብሔር ያድናችኋል፤ ከጠላቶቻችሁም እጅ ይታደጋችኋል። 11አሁን ግን ብዙ ሕዝቦች በእናንተ ላይ ተሰብስበው እንዲህ ይላሉ፦ “ኢየሩሳሌም ትርከስ! እኛም መፍረስዋን እንይ!” 12እነዚህ ሕዝቦች ግን የእግዚአብሔርን ዕቅድ አላወቁም፤ የሚወቃ የእህል ነዶ በአውድማ ላይ እንደሚሰበሰብ እግዚአብሔር እነርሱን ራሳቸውን የሰበሰባቸው ለቅጣት መሆኑን አልተገነዘቡም።
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ሂዱና ጠላቶቻችሁን እንደ እህል አበራዩ! ቀንዱ ብረት፥ ሰኮናው ነሐስ እንደ ሆነ በሬ ብርቱ አደርጋችኋለሁ፤ ብዙ መንግሥታትን ትደመስሳላችሁ፤ እነርሱ በግፍ የሰበሰቡትን ሀብትና ንብረት ሁሉ ለመላው ዓለም ጌታ ለእኔ ለእግዚአብሔር አምጥታችሁ ታቀርባላችሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997