YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 22

22
የሠርጉ ግብዣ ምሳሌ
(ሉቃ. 14፥15-24)
1እንደገናም ኢየሱስ በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ነበር፤ 2“መንግሥተ ሰማይ ለልጁ የሠርግ ድግስ የደገሰውን ንጉሥ ትመስላለች። 3ንጉሡ የተጠሩትን ሰዎች ወደ ሠርጉ እንዲመጡ ለማሳሰብ አገልጋዮቹን ወደ እነርሱ ላከ፤ ሰዎቹ ግን ወደ ሠርጉ ሊመጡ አልፈለጉም።
4“ንጉሡ ሌሎች አገልጋዮችን እንደገና እንዲህ ሲል ላከ፤ ‘ወደ ተጠሩት ሰዎች ሂዱና፦ እነሆ፥ የሠርግ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶአል፤ ስለዚህ ወደ ሠርጉ ግብዣ ኑ!’ ብላችሁ ንገሩአቸው። 5እነርሱ ግን ነገሩን ችላ ብለው በየፊናቸው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6የቀሩትም ደግሞ አገልጋዮቹን ይዘው በማዋረድ ደበደቡና ገደሉአቸው፤ 7በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተቈጣና ወታደሮቹን ልኮ እነዚያን ገዳዮች አስገደለ፤ ከተማቸውንም በእሳት እንዲያቃጥሉ አደረገ፤ 8ከዚህ በኋላ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘እነሆ፥ የሠርጉ ድግስ ተዘጋጅቶአል፤ የተጠሩት ግን ለግብዣው የተገቡ አልሆኑም። 9ስለዚህ በየአውራ ጐዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ግብዣ ጥሩ።’ 10አገልጋዮቹም በየመንገዱ ሄደው፥ ያገኙትን ሰው ሁሉ ክፉዎችንም፥ ደጎችንም ሰበሰቡ፤ ስለዚህ የሠርጉ አዳራሽ በተጋባዦች ተሞላ።
11“ነገር ግን ንጉሡ ተጋባዦቹን ለማየት ወደ አዳራሽ በገባ ጊዜ፥ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው በዚያ አየ። 12እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ ሰውየው ግን ዝም አለ። 13ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ ‘እጅና እግሩን እሰሩና አውጥታችሁ በውጪ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አለ።” #ማቴ. 8፥12፤ 25፥30፤ ሉቃ. 13፥28። 14ቀጥሎም ኢየሱስ “ስለዚህ የተጠሩ ብዙዎች ናቸው፤ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” አለ።
ግብር ስለ መክፈል የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 12፥13-17ሉቃ. 20፥20-26)
15ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው ኢየሱስን በንግግሩ እንደሚያጠምዱት ተማከሩ፤ 16የእነርሱንም ደቀ መዛሙርት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ወደ ኢየሱስ ልከው፥ “መምህር ሆይ! አንተ እውነተኛ መሆንህንና የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራት የምታደርገው ነገር የለም፤ ለሰውም አታዳላም” ካሉት በኋላ፥ እንዲህ ብለው ጠየቁት። 17“በል እስቲ ንገረን ምን ይመስልሃል? ለሮማው ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን ወይስ አይደለም?” 18ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን ዐውቆ፥ “እናንተ ግብዞች! ስለምን ትፈትኑኛላችሁ? 19ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ!” አላቸው። ስለዚህ እነርሱ አንድ ዲናር አምጥተው አሳዩት። 20እርሱም፥ “በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ 21እነርሱም፥ “የሮማው ንጉሠ ነገሥት ነው!” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤” አላቸው። 22እነርሱም ከሰሙት በኋላ በአነጋገሩ ተደንቀው ትተውት ሄዱ።
ስለ ሙታን መነሣት የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 12፥18-27ሉቃ. 20፥27-40)
23በዚያኑ ቀን፥ “የሙታን ትንሣኤ የለም” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ #ሐ.ሥ. 23፥8። 24“መምህር ሆይ! ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አግብቶ ለሟቹ ዘር ይተካለት፤’ ብሎአል። #ዘዳ. 25፥5። 25ሰባት ወንድማማቾች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ስለዚህ ታናሽ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። 26እንዲሁ ሁለተኛውም፥ ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ በየተራ አግብተዋት ሞቱ። 27ከሁሉም በኋላ ሴትዮዋ ሞተች። 28ታዲያ፥ ሰባቱም ስለ አገቡአት ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
29ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቃችሁ ትሳሳታላችሁ። 30በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ሰዎች በሰማይ እንዳሉት መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። 31ደግሞ ስለ ሙታን መነሣት እግዚአብሔር ለእናንተ የነገራችሁን አላነበባችሁምን? 32እርሱም ያለው እንዲህ ነው፦ ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” #ዘፀ. 3፥6። 33ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ በትምህርቱ ተደነቁ።
ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ
(ማር. 12፥28-34ሉቃ. 10፥25-28)
34ኢየሱስ ሰዱቃውያንን መልስ አሳጥቶ ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ። 35ከእነርሱም አንድ የሕግ መምህር፥ ኢየሱስን ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ #ሉቃ. 10፥25-28። 36“መምህር ሆይ! ከሕግ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” 37ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ አምላክህን በሙሉ ልብህ፥ በሙሉ ነፍስህ፥ በሙሉ ሐሳብህ ውደድ፤ #ዘዳ. 6፥5። 38ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው። 39ይህንንም የሚመስለው ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚለው ነው። #ዘሌ. 19፥18። 40የሕግና የነቢያት ትምህርት ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዞች ላይ ነው።”
ስለ መሲሕ የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 12፥35-37ሉቃ. 20፥41-44)
41ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ 42“ስለ መሲሕ ምን ትላላችሁ? የማንስ ልጅ ይመስላችኋል?” እነርሱም “የዳዊት ልጅ ነው” ሲሉ መለሱለት። 43ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ታዲያ፥ ዳዊት በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ በተናገረ ጊዜ እንዴት ‘ጌታ’ ብሎ ጠራው?
44‘እግዚአብሔር ለጌታዬ
ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ
በቀኜ ተቀመጥ!’ አለው። #መዝ. 110፥1።
45እንግዲህ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ መሲሕ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” 46በዚህ አንድ ቃል እንኳ ሊመልስለት የቻለ ማንም ሰው አልነበረም፤ ከዚያን ቀን ጀምሮም ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም አልነበረም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in