YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 21

21
የኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባት
(ማር. 11፥1-11ሉቃ. 19፥28-40ዮሐ. 12፥12-19)
1ኢየሱስና ተከታዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜ በደብረ ዘይት ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደምትባለው መንደር ሲደርሱ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ 2“በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ እዚያም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ ወዲያውኑ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። 3ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢላችሁ ‘ጌታ ስለሚፈልጋቸው ነው’ በሉት። እርሱም አህዮቹን ወዲያውኑ ይልካቸዋል።” 4ይህም የሆነው በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፦
5“የጽዮን ከተማ ለምትባለው ለኢየሩሳሌም፦
‘እነሆ! ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያይቱና
በውርንጫዋ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል!’ ብላችሁ ንገሩአት።” #ዘካ. 9፥9።
6ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7አህያዋንም ከነውርንጫዋ አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በአህዮቹ ጀርባ ላይ አደረጉ፤ ኢየሱስም በዚያ ላይ ተቀመጠ። 8ከሕዝቡም ብዙዎቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቀጠፉ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። 9ከሕዝቡም ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትና ከኋላ ይከተሉ የነበሩት፥ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይሁን! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና! ምስጋና በአርያም ለእግዚአብሔር ይሁን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። #21፥9 ሆሳዕና፦ በዕብራይስጥ ቋንቋ መዳን፥ አቤቱ አድነን ማለት ነው። #መዝ. 118፥25-26። 10ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የከተማው ሰዎች በሙሉ “ይህ ማን ነው?” በማለት ታወኩ። 11ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ምድር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ።
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ የሚገበያዩትን እንዳስወጣ
(ማር. 11፥15-19ሉቃ. 19፥45-48ዮሐ. 2፥13-22)
12ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ሁሉ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ። 13“ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። #ኢሳ. 56፥7፤ ኤር. 7፥11።
14ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሳለ ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡና ፈወሳቸው። 15ነገር ግን የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስ ያደረገውን ድንቅ ነገር በማየታቸውና ሕፃናትም በቤተ መቅደስ “ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና! ምስጋና ይሁን!” እያሉ ሲጮኹ በመስማታቸው ተቈጡ። 16ስለዚህ ኢየሱስን “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት፤ እርሱም “አዎ፥ እሰማለሁ፤ ‘ከልጆችና ከሚጠቡት ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው፤ #መዝ. 8፥2። 17ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ቢታንያ ወደምትባል መንደር ሄደ፤ በዚያም ዐደረ።
ኢየሱስ የረገማት የበለስ ዛፍ
(ማር. 11፥12-1420-24)
18ኢየሱስ ጠዋት በማለዳ፥ ወደ ከተማ ተመልሶ ሲሄድ ራበው፤ 19አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች። 20ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ይህች የበለስ ዛፍ በአንድ አፍታ እንዴት ደረቀች!” በማለት ተገረሙ። 21ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ በበለሲቱ ዛፍ ላይ እንደ ተደረገው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህንን ተራራ እንኳ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር!’ ብትሉት ይሆንላችኋል። #ማቴ. 17፥20፤ 1ቆሮ. 13፥2። 22አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።”
ኢየሱስ በምን ሥልጣን እንደሚሠራ የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 11፥27-33ሉቃ. 20፥1-8)
23ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ያስተምር ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀረቡና “ይህን ሁሉ የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 24ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ ለጥያቄዬ መልስ ከሰጣችሁኝ እኔም ይህን ሁሉ በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 25የዮሐንስ ጥምቀት ከየት መጣ? ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው?” እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም’ ይለናል፤ 26‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት፥ ሕዝቡን እንፈራለን።” 27ስለዚህ “አናውቅም” ሲሉ ለኢየሱስ መለሱለት። እርሱም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን ሁሉ እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።
የሁለቱ ልጆች ምሳሌ
28ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ታዲያ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ከእነርሱ ወደ አንደኛው ቀርቦ፥ ‘ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ወደ ወይን አትክልት ቦታዬ ሄደህ እንድትሠራ ይሁን’ አለው። 29ልጁም ‘እምቢ አልሄድም’ አለ። ይሁን እንጂ በኋላ ተጸጸተና ሊሠራ ሄደ። 30አባትየው ወደ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ ሄደና እርሱንም እንዲሁ እንዲሠራ አዘዘው፤ ልጁም ‘እሺ አባቴ እሄዳለሁ’ አለ። ነገር ግን አልሄደም። 31እንግዲህ ከነዚህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?”
እነርሱም “የመጀመሪያው ነዋ!” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ወደ መንግሥተ ሰማይ በመግባት ይቀድሙአችኋል። 32መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ቢመጣ አላመናችሁትም፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ ይህንንም አይታችሁ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።” #ሉቃ. 3፥12፤ 7፥29-30።
የወይኑ አትክልት ገበሬዎች ምሳሌ
(ማር. 12፥1-12ሉቃ. 20፥9-19)
33ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ በወይኑ አትክልት ዙሪያ አጥር ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ረዥም ግንብ ሠራ፤ ከዚህ በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። #ኢሳ. 5፥1-2። 34የፍሬ ወራት በደረሰ ጊዜ ድርሻውን እንዲቀበሉለት አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 35ገበሬዎቹ ግን አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። 36የወይኑ አትክልት ባለቤት እንደገና ቊጥራቸው ከፊተኞቹ የሚበልጥ ሌሎችን አገልጋዮች ደግሞ ላከ። ገበሬዎቹ በእነርሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። 37በመጨረሻም የወይኑ አትክልት ጌታ ‘ልጄንስ ያከብሩታል!’ በማለት ልጁን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 38ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እኛ እንውረስ!’ ተባባሉ። 39ልጁንም ይዘው ከወይን አትክልቱ ቦታ ውጪ ወሰዱና ገደሉት።
40“ታዲያ፥ የወይኑ አትክልት ባለቤት በመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” 41እነርሱም “የእነዚህን ክፉ ሰዎች ፍጻሜ የከፋ ያደርገዋል። የወይኑንም ተክል ቦታ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት።
42ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤
“በቅዱሳት መጻሕፍት
‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ
እርሱ ዋና የማእዘን ራስ ሆነ፤
ይህም የጌታ ሥራ ነው፤
ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’
ተብሎ የተጻፈውን ከቶ አላነበባችሁምን? #መዝ. 118፥22-23።
43“ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬ ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። [ 44በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።”] #21፥44 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቁ. 44 ይጨምራሉ፤ ቃሉም በሉቃ. 20፥18 ያለውን ይመስላል።
45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን እነዚህን ምሳሌዎች በሰሙ ጊዜ ኢየሱስ የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ተገነዘቡ። 46ስለዚህ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያየው ስለ ነበር ፈሩ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in