መጽሐፈ ኢዮብ 12
12
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“በእርግጥ እናንተ በጣም ብልኆች ናችሁ፤
ስትሞቱም ጥበብ ከእናንተ ጋር የምትሞት ይመስላችኋል!
3ይሁን እንጂ
እኔም የእናንተን ያኽል ማስተዋል አለኝ፤
ከቶ ከእናንተ በምንም አላንስም፤
እናንተ የተናገራችሁትን ሰው ሁሉ ያውቀዋል።
4እግዚአብሔርን ጠርቼው የመለሰልኝ ጊዜ ነበር፤
አሁን እኔ የወዳጆቼ መሳቂያ ሆኛለሁ፤
ስሕተት የሌለብኝ ፍጹሙ እኔ የሰው ሁሉ መሳለቂያ ሆኛለሁ።
5ችግር ባልደረሰበት ሰው ዘንድ
የተቸገረን ሰው ችግር ማናናቅ ቀላል ነው።
ነገር ግን ሊወድቅ የሚንገዳገደውን ሰው ትገፈትሩታላችሁ።
6ኀይላቸውን እንደ አምላክ አድርገው የሚቈጥሩ
ሌቦችና እግዚአብሔርን የካዱ ሰዎች እንኳ በሰላም ይኖራሉ።
7“ነገር ግን እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩሃል፤
የሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩህማል።
8ወይም ለምድር ተናገር፤ እርስዋም ታስተምርሃለች፤
የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።
9ከእነዚህ ሁሉ መካከል የእግዚአብሔር እጅ ይህን
እንደ ሠራ የማያውቅ ማነው?
10ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉና
የእያንዳንዱም ሰው ነፍስ በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ነው።
11ምላስ የምግብን ጣዕም ለይቶ እንደሚያውቅ፥
ጆሮም የንግግርን ዐይነት መርምሮ ይለያል።
12“ጥበብ በሽምግልና፥
ማስተዋልም በዕድሜ መርዘም ይገኛሉ።
13እግዚአብሔር ግን ጥበብና ኀይል አለው፤
ምክርና አስተዋይነት የሚገኙት ከእርሱ ነው።
14እግዚአብሔር ያፈረሰውን ማንም መልሶ መሥራት አይችልም፤
እግዚአብሔር ያሰረውንም ማንም ሊፈታው አይችልም፤
15እግዚአብሔር ዝናብን ቢከለክል ድርቅ ይሆናል፤
ዝናብን ቢለቅ ግን ምድር በጐርፍ ትጥለቀለቃለች።
16እግዚአብሔር ብርቱና ድል አድራጊ ነው፤
የሚታለልም ሆነ የሚያታልል
ሁለቱም በእርሱ ሥልጣን ሥር ናቸው።
17እርሱ አማካሪዎችን ጥበብ ይነሣቸዋል፤
የሕዝብ መሪዎችንም ሞኞች ያደርጋቸዋል።
18እርሱ ነገሥታትን ከዙፋናቸው ያወርዳል፤
ሽርጥ የታጠቁ እስረኞችም ያደርጋቸዋል።
19ካህናትን ሥልጣናቸውን ገፎ ያባርራቸዋል፤
ባለሥልጣኖችን ከሥልጣናቸው ያስወግዳቸዋል።
20የታመኑትን ሰዎች ዝም ያሰኛቸዋል፤
ከሽማግሌዎችም አስተዋይነትን ይነሣል።
21መኳንንትን ያሳፍራቸዋል፤
የኀያላንን ኀይል ያስወግዳል።
22በጨለማ የተሰወረውን ምሥጢር ይገልጣል፤
ድቅድቅ ጨለማን ወደ ብርሃን ይለውጣል።
23መንግሥታትንም ታላላቅ ያደርጋቸዋል፤ ያጠፋቸዋልም፤
ሕዝብን ያበዛል፤ ይበታትናልም።
24መሪዎች ማስተዋል እንዲጐድላቸውና
መንገድ በሌለበት በበረሓ እንዲቅበዘበዙ ያደርጋል።
25ብርሃን አጥተው በጨለማ እንዲደናበሩና
እንደ ሰከረም ሰው እንዲንገዳገዱ ያደርጋቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 12: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997