ትንቢተ ኤርምያስ 13
13
ከተልባ ቃጫ የተሠራ መታጠቂያ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ከበፍታ የተሠራ መታጠቂያ ገዝተህ ታጠቀው፤ ውሃ ግን አታስነካው።” 2ስለዚህ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት መታጠቂያውን ገዝቼ ታጠቅሁት፤ 3እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦ 4“ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ሂድና መታጠቂያውን በአለት ንቃቃት ውስጥ ደብቀው።” 5ስለዚህ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ሄጄ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መታጠቂያውን ደበቅሁት።
6ከብዙ ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር፥ “ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተመልሰህ ሂድና መታጠቂያውን ውሰድ” አለኝ። 7እኔም ሄጄ መታጠቂያውን የደበቅሁበትን ስፍራ አገኘሁ፤ መታጠቂያውንም ባየሁት ጊዜ ተበላሽቶና ከጥቅም ውጪ ሆኖ አገኘሁት።
8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 9“የይሁዳን ኲራትና የኢየሩሳሌምን ታላቅ ትዕቢት የማስወግደው በዚህ ዐይነት ነው፤ 10እነዚህ በክፋት የተሞሉ ሕዝብ ለእኔ መታዘዝን እምቢ ብለዋል፤ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኞች ሆነዋል፤ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ያገለግላሉ፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ ዋጋቢስ ሆኖ እንደ ቀረው እንደዚያ መታጠቂያ ይሆናሉ። 11መታጠቂያ በወገብ ዙሪያ ተጣብቆ እንደሚገኝ፥ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ከእኔ ጋር እንዲጣበቁ ዐቅጄ ነበር፤ ይህንንም ያደረግኹት ሕዝቤ እንዲሆኑና ለስሜ ምስጋናና ክብር እንዲያስገኙ ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙኝም።”
የወይን ጠጅ ማድጋ
12እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አለኝ፦ “ኤርምያስ ሆይ! ‘እያንዳንዱ ማድጋ በወይን ጠጅ የተሞላ ይሆናል’ ብለህ ለእስራኤል ሕዝብ ንገር፤ በዚያን ጊዜ እነርሱ ‘ማድጋ በወይን ጠጅ መሞላቱን የማናውቅ ይመስልሃልን?’ ይሉሃል። 13ከዚህ በኋላ እኔ እግዚአብሔር በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ እስከሚሰክሩ ድረስ በወይን ጠጅ ልሞላቸው እንዳቀድኩ ንገራቸው፤ በዚያን ጊዜ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታትን፥ ካህናትን፥ ነቢያትንና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችን ሁሉ በወይን ጠጅ አሰክራቸዋለሁ። 14ያን ጊዜ አባቶችንና ልጆቻቸውን ሁሉንም እንደ ማድጋ እርስ በርሳቸው አጋጫቸዋለሁ፤ ምንም ዐይነት ሐዘኔታ፥ ርኅራኄ ወይም ምሕረት እነርሱን ከማጥፋት ሊያግደኝ አይችልም።”
ስደት እንደሚመጣ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
15እግዚአብሔር ተናግሮአልና፤
ትዕቢታችሁን አስወግዳችሁ ስሙት፤
በጥንቃቄም አድምጡት።
16ጨለማን አምጥቶ በተራራዎች ከመሰናከላችሁ በፊት
ተስፋ ያደረጋችኹትን ብርሃን
ወደ ድቅድቅ ጨለማና ወደ ጥልቅ ጭጋግ ከመለወጡ በፊት
አምላካችሁን እግዚአብሔርን አክብሩ።
17አናዳምጥም ብትሉ ግን
ስለ ትዕቢታችሁ ተደብቄ አለቅሳለሁ፤
የእግዚአብሔር ሕዝብ ምርኮኞች ሆነው በመወሰዳቸውም
ምርር ብዬ አለቅሳለሁ፤ እንባዬም ባለማቋረጥ ይፈስሳል።
18እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የተከበረ ዘውዳቸው ከራሳቸው ስለ ወደቀ ንጉሡና ንግሥት እናቱ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ ንገራቸው። 19በደቡብ ይሁዳ ያሉት ከተሞች በጠላት ስለ ተከበቡ ማንም ወደ እነርሱ ሊሄድ አይችልም፤ መላው የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ይወሰዳሉ።”
20ኢየሩሳሌም ሆይ! ከሰሜን በኩል የጠላቶችሽን አመጣጥ ተመልከቺ፤ ስትንከባከቢያቸው የነበርሽና መመኪያዎችሽ የነበሩ ሕዝብ የት ደረሱ? 21ወዳጆች ብለሽ ያቀረብሻቸው ወራሪዎችሽና ገዢዎችሽ ሲሆኑ ምን ትያለሽ? በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ሕመም አይሰማሽምን? 22ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ለምንድነው? “ልብሴስ ተቀዶ የተደፈርኩት ስለምንድነው?” ብለሽ ብትጠይቂ፤ ይህ ሁሉ የደረሰብሽ ኃጢአትሽ እጅግ የከፋ በመሆኑ ምክንያት እንደ ሆነ ዕወቂ። 23ኢትዮጵያዊ መልኩን፥ ነብርም ዝንጒርጒርነቱን መለወጥ አይችልም፤ እንዲሁም እናንተ ክፉ ነገር ማድረግን ስለ ለመዳችሁ ደግ ሥራ መሥራት አይሆንላችሁም። 24አሁን ግን እግዚአብሔር የበረሓ ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ገለባ ይበታትናችኋል። 25ዕድል ፈንታችሁም ይህ እንደሚሆን እግዚአብሔር ተናግሮአል። እርሱን ረስታችሁ በሐሰተኞች አማልክት ስለ ታመናችሁ በእናንተ ላይ ይህን ለማድረግ ወስኖአል። 26እግዚአብሔር ራሱ ልብሳችሁን ገፎ ኀፍረተ ሥጋችሁ እንዲጋለጥ ያደርጋል። 27እርሱ የሚጠላውን ነገር ስታደርጉ አይቶአችኋል፤ ከባልንጀራው ሚስት ጋር ለማመንዘር እንደሚጐመጅ ሰውና ባዝራ እንደሚፈልግ ሰንጋ ፈረስ፥ እናንተም የአሕዛብ አማልክትን ተከትላችሁ በየኰረብታው ራስና በየሜዳው ስትኳትኑ አይቶአችኋል። የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፥ ወዮላችሁ፥ ከቶ ንጹሕ መሆን የምትችሉት መቼ ይሆን?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 13: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997