ትንቢተ ኤርምያስ 12
12
የኤርምያስ ጥያቄ
1እግዚአብሔር ሆይ! ከአንተ ጋር በምከራከርበት ጊዜ ሁሉ አንተ ትክክለኛ ነህ፤
አሁን ግን ስለ ትክክለኛ ፍርድ ጥያቄ አለኝ፤
የኃጢአተኛ ሕይወት የተቃና የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?
አታላዮችስ ሁሉ ነገር የሚሳካላቸው ስለምንድን ነው?
2አንተ ተክለሃቸዋል፤ እነርሱም ሥር ሰደዋል፤
አድገውም ፍሬ ያፈራሉ፤
በአፋቸው ያከብሩሃል፤
ልባቸው ግን ከአንተ የራቀ ነው።
3እግዚአብሔር ሆይ! እኔን ግን ታውቀኛለህ፤
ስለ አንተ ያለኝን አስተሳሰብ አይተህ ትፈትነኛለህ፤
እነዚህን ክፉ ሰዎች እንደሚታረዱ በጎች ውሰዳቸው፤
ለዕርድም ቀን ለይተህ አቈያቸው።
4“እኛ የምናደርገውን ሁሉ እግዚአብሔር አያይም” ከሚሉት ሕዝባችን ክፋት የተነሣ፥
ምድራችንን ድርቅ የሚያጠቃውና
በየመስኩ ያለውስ ሣር እንደ ደረቀ የሚቀረው እስከ መቼ ነው?
በዚህም ምክንያት እንስሶችና ወፎች ሁሉ ተጠራርገው ጠፍተዋል።
የእግዚአብሔር መልስ
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ኤርምያስ ሆይ! በእግር ሩጫ ከሰዎች ጋር መወዳደር የሚያደክምህ ከሆነ፥
ከፈረስ ጋር መወዳደር እንዴት ትችላለህ?
ግልጥ በሆነው ሜዳ ላይ ጸንተህ መቆም ካቃተህ፥
በዮርዳኖስ ደን ውስጥ መቆም እንዴት ትችላለህ?
6ወንድሞችህና የቅርብ ዘመዶችህ ከድተውሃል፤
በአንተ ላይ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፤
ስለዚህ በፊትህ ስለ አንተ መልካም ነገር ቢናገሩም አትመናቸው።”
የሕዝቡ በደል እግዚአብሔርን ማሳዘኑ
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ቤቴንና ርስቴን ትቼአለሁ፤
የምወዳቸውን ሕዝቤንም
ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
8ሕዝቤ በእኔ ላይ ተነሥተው እንደ ዱር አንበሳ ያገሡብኛል፤
ይህንንም አድራጎታቸውን እጠላለሁ።
9የመረጥኳቸው ሕዝቤ በሁሉ አቅጣጫ በጭልፊቶች እንደ ተከበበች ወፍ ሆነዋል፤
ስለዚህ ሌሎችም የዱር አራዊት መጥተው ሥጋቸውን በመብላት እንዲደሰቱ ጥሩአቸው።
10ብዙ መሪዎች የወይን ተክል ቦታዬን አጥፍተዋል፤
የእርሻ ቦታዎቼንም ረጋግጠዋል፤
ደስ የምታሰኘውን ምድሬንም ወደ በረሓነት ለውጠዋታል።
11ምድረ በዳም ስላደረጉአት በፊቴ ባድማ ሆናለች፤
አገሪቱ በሙሉ ወደ በረሓነት ተለውጣለች፤
ስለ እርስዋም የሚገደው አንድ እንኳ የለም።
12በረሓማ ከሆነው ከባዶ ተራራ አጥፊዎች ይመጣሉ፤
የእግዚአብሔር ሰይፍ ሀገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ስለሚያጠፋ
አንድም ሰው አይድንም።
13ሕዝቤ ስንዴ ዘርተው እሾኽ ሰበሰቡ፤
በሥራ እጅግ ደክመው ምንም ትርፍ አላገኙም፤
ከብርቱ ቊጣዬ የተነሣ በምርታቸው መጥፋት አዘኑ።”
እግዚአብሔር ለእስራኤል ጐረቤቶች የሰጠው የተስፋ ቃል
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለሕዝቤ ለእስራኤል የሰጠኋቸውን ምድር ስላጠፉት ስለ እስራኤል ጐረቤቶችም የምናገረው ነገር አለኝ፤ እነዚያን ክፉ ሕዝቦች ከየአገራቸው ነቃቅዬ እወስዳቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ሕዝብ ከመካከላቸው መንጥቄ አወጣቸዋለሁ። 15ነገር ግን ከአገራቸው ካወጣኋቸው በኋላ እንደገና ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ እያንዳንዱንም ሕዝብ ወደ ገዛ ምድሩና ወደ ገዛ አገሩ መልሼ አመጣዋለሁ። 16የሕዝቤን አካሄድ በሙሉ ልባቸው ተቀብለው እነርሱ ከዚህ በፊት ሕዝቤን በባዓል ስም መማል እንዳስተማሩአቸው ዐይነት ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው የሚምሉ ከሆነ በሕዝቤ መካከል እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ፤ 17ከእነርሱ መካከል የማይሰማኝ ሕዝብ ቢኖር ግን ነቃቅዬ አጠፋዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 12: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997