ትንቢተ ኢሳይያስ 51
51
ዘለዓለማዊ ደኅንነት ለኢየሩሳሌም
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እኔንና ጽድቅን የምትፈልጉ አድምጡኝ፤
ወደ ተጠረባችሁበት ድንጋይና
ወደ ወጣችሁበት ጒድጓድ ተመልከቱ።
2ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃምና
ወደ ወለደቻችሁ ወደ ሣራ ተመልከቱ፤
አብርሃምን በጠራሁት ጊዜ ልጅ አልነበረውም፤
ነገር ግን እኔ ባረክሁት፤
ዘሩንም አበዛሁለት።
3“እኔ እግዚአብሔር ጽዮንንና ባድማ የሆኑባትን ቦታዎችዋን ሁሉ አጽናናለሁ፤
ምድረ በዳዋን እንደ ዔደን፥ በረሓዋንም እንደ ገነት አደርጋለሁ፤
በእርስዋም ተድላና ደስታ ይገኛል፤
እንዲሁም የምስጋና መዝሙር ድምፅ ይሰማል።
4“ሕዝቤ ሆይ! ስሙ! የምላችሁንም አድምጡ
ሕግ ከእኔ ይገኛል፤
ፍርዴም ለሕዝቦች ሁሉ ብርሃን ይሆናል።
5ፈጥኜ በመምጣት አድናቸዋለሁ፤
በቅጽበት ድል የምነሣበት ጊዜ ይመጣል፤
በኀይሌ ሕዝቦችን ሁሉ እገዛለሁ፤
በደሴቶች የሚኖሩ ሕዝቦች፥
እኔን በተስፋ ይጠባበቃሉ፤
ኀይሌንም ተስፋ ያደርጋሉ።
6ቀና ብላችሁ ወደ ሰማያት ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤
ሰማያት እንደ ጢስ በነው ይጠፋሉ፤
ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፤
በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ እንደ ዝንብ ይሞታሉ፤
የእኔ ማዳን ግን ዘለዓለማዊ ነው፤
ለታዳጊነቴም ፍጻሜ የለውም።
7“እናንተ ትክክለኛውን ነገር የምታውቁና
ሕጌ በልባችሁ ያለ ሰዎች አድምጡኝ፤
የሰዎችን ነቀፋ አትፍሩ፤ ወይም በስድባቸው አትደናገጡ።
8እነርሱ ብል እንደ በላው ልብስና
ትል እንደበላው ሱፍ ይሆናሉ፤
የእኔ ታዳጊነት ግን ዘለዓለማዊ ነው፤
አዳኝነቴም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል።”
9እግዚአብሔር ሆይ! ተነሥ፤ ተነሥተህ ኀይልህን ግለጽ!
በጥንት ዘመን በነበረው ትውልድ መካከል እንዳደረግኸው ተነሥ፤
ረዓብ የተባለውን የባሕር ዘንዶ ቈራርጠህ ያደቀቅከው አንተ ነህ።
10አንተ ያዳንካቸው ይሻገሩበት ዘንድ ባሕሩንና ጥልቁን ውሃ አድርቀህ
መንገድ ያደረግህላቸው አንተ ነህ።
11ስለዚህ አንተ እግዚአብሔር የተቤዠኻቸው
እየዘመሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሳሉ፤
ዘላቂ ደስታንም እንደ ዘውድ ይቀዳጃሉ፤
ሐሴትና ደስታንም ያገኛሉ፤
ማዘንና መቃተት ግን ከእነርሱ ይወገዳል።
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥
“የማጽናናችሁ እኔ ራሴ ነኝ፤
ታዲያ እንደ ሣር የሚጠወልገውንና
መሞት ያለበትን ሰውን የምትፈሩት ለምንድን ነው?
13ምድርን የመሠረተና ሰማያትን የዘረጋ
ፈጣሪአችሁን እግዚአብሔርን ረስታችኋል፤
ሊያጠፉአችሁ ከተዘጋጁ ከጨቋኞቻችሁ ቊጣ የተነሣ፥
ዘወትር በፍርሃት ትኖራላችሁ።
የእነርሱስ ቊጣ የት አለ?
14እስረኞች በፍጥነት ነጻ ይወጣሉ፤ አይሞቱም፤
ወደ ጥልቁ ጒድጓድም አይወርዱም።
የሚበሉትንም እንጀራ አያጡም።
15“ማዕበሉ ይጮኽ ዘንድ ባሕሩን የማናውጥ
እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤
ስሜም የሠራዊት አምላክ ነው።
16ቃሌን በአንደበትሽ አሳድራለሁ፤
አንቺንም በእጄ ጥላ ሥር እጋርድሻለሁ፤
ሰማያትን የዘረጋሁ፥ ምድርንም የመሠረትኩ እኔ ነኝ፤
ጽዮንንም ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’ እላታለሁ።”
የእግዚአብሔር የቊጣ ጽዋ
17አንቺ ከእግዚአብሔር እጅ የሚያንገዳግደውን የቊጣውን ጽዋ
በትልቅ ዋንጫ ጨልጠሽ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ!
ንቂ፤ ተነሥተሽም ቁሚ! #ራዕ. 14፥10፤ 16፥19።
18የሚመራሽ ከቶ የለም፤
ከወለድሻቸውና ካሳደግሻቸው ልጆች ሁሉ
እጅሽን ይዞ የሚመራሽ አልተገኘም።
19ውድመትና ጥፋት፥ ራብና ጦርነት፥
እነዚህ ሁለት ነገሮች ደርሰውብሻል፤
የሐዘንሽ ተካፋይ የሚሆን ማነው?
ማንስ ያጽናናሻል?
20ልጆችሽ በወጥመድ ውስጥ እንደ ተያዘ ድኩላ
በየመንገዱ አደባባይ ተዝለፍልፈው ወድቀዋል፤
በእነርሱም ላይ የአምላክሽ የእግዚአብሔር ተግሣጽና ቊጣ ወርዶባቸዋል።
21ስለዚህ በወይን ጠጅ ሳይሆን
በችግር የሰከራችሁ እናንተ ይህን ስሙ።
22የሕዝቡን አቤቱታ የሚመለከተው አምላካችሁ
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እንደ ሰከረ ሰው የሚያንገዳግደውን የመከራ ጽዋ ከእጃችሁ ወስጄአለሁ፤
ከእንግዲህ ወዲያ ኀይለኛ ቊጣዬን ከትልቁ ዋንጫ አትጠጡም።
23የመከራውንም ጽዋ ‘አጐንብሺና በጀርባሽ እንራመድብሽ’
ለሚሉና አንቺን ለሚያሠቃዩ ሰዎች በእጃቸው እሰጣለሁ፤
አንቺም እነርሱ ይራመዱብሽ ዘንድ ጀርባሽን
እንደ መሬትና እንደ መንገድ አድርገሻል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 51: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997