YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 52

52
እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይታደጋታል
1ጽዮን ሆይ! ተነሺ፤ ንቂ!
ኀይልሽን እንደ ልብስ ልበሺ!
ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ!
የተዋበ ልብስሽን ልበሺ፤
ከእንግዲህ ወዲህ ያልተገረዙና በሥርዓት ያልነጹ ሰዎች ወደ ቅጥርሽ ውስጥ አይገቡም። #ራዕ. 21፥2፤27።
2ምርኮኛይቱ ኢየሩሳሌም ሆይ!
ተነሥተሽ ትቢያሽን አራግፊ፤
በዙፋን ላይም ተቀመጪ፤
እናንተም የጽዮን ምርኮኞች ሆይ!
የታሰራችሁበትን ሰንሰለት ከአንገታችሁ ፍቱ።
3እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲህ ይላል፦ “ለባርነት ያለ ዋጋ ተሸጣችሁ ነበር፤ የምትዋጁትም ዋጋ ሳይከፈል ነው። 4ከዚህ በፊት ወደ ግብጽ ወርዳችሁ በስደት የኖራችሁት በፈቃዳችሁ ነበር፤ አሦራውያን ግን ምንም ሳይከፍሉባችሁ ማርከው በመውሰድ በብርቱ ጨቊነው ገዙአችሁ”። 5“ሕዝቤ ያለ ዋጋ ሲወሰድ እያየሁ አሁን እኔ የማደርገው ምን አለ? ገዢዎቻቸውም ይሳለቁባቸዋል፤ ያለማቋረጥም ስሜን ይሰድባሉ። #ሮም 2፥24። 6ስለዚህ በዚያን ጊዜ ሕዝቤ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን፥
ይህንንም የምናገረው እኔ መሆኔን ያውቃሉ።”
7በተራሮች ላይ ስለ ሰላምና ስለ መዳን የሚናገር፥
መልካም ዜናንም የሚያበሥር፥
“አምላክሽ ይነግሣል!” ብሎ ለጽዮን የሚነግራት
የመልክተኛ እግሩ ምንኛ ድንቅ ነው! #ናሆም 1፥15፤ ሮም 10፥15፤ ኤፌ. 6፥15።
8እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስ በግልጽ ስለሚያዩ
ከተማ ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው
የደስታ መዝሙር ሲዘምሩ አድምጪ።
9እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል
ኢየሩሳሌምንም ይታደጋል
ስለዚህ እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ!
ተባብራችሁ በደስታ ዘምሩ።
10እግዚአብሔር በሕዝቦች ሁሉ ፊት ኀያልነቱን ይገልጣል፤
መላው ዓለምም የእርሱን አዳኝነት ያያል።
11እናንተ የቤተ መቅደስን ንዋያተ ቅድሳት የተሸከማችሁ!
ከባቢሎን ውጡ፤ ከእርሱም ተለዩ፤
ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤
ከመካከልዋም ወጥታችሁ ራሳችሁን አንጹ። #2ቆሮ. 6፥17።
12እግዚአብሔር በፊታችሁ ሆኖ ስለሚመራችሁ፥
የእስራኤል አምላክ ከበኋላ ሆኖ ስለሚጠብቃችሁ
ስትወጡም በችኰላና በመኰብለል አይሆንም።
መከራ የሚደርስበት አገልጋይ
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እነሆ፥ አገልጋዬ ሥራው ሁሉ ይከናወንለታል፤
በክብርም እጅግ ከፍ ከፍ ይላል።
14ከማንኛውም ሰው በላይ መልኩ በጣም ተጐሳቊሎ ስለ ነበረ
ሁናቴውን ያዩ ሰዎች አብዛኞቹ በጣም ደነገጡ።
15ቀድሞ ያልተነገራቸውን ነገር ስለሚያዩና
ያልሰሙትን ነገር ስለሚያስተውሉ
ብዙ ሕዝቦች ስለ አገልጋዬ ይደነቃሉ፤
ነገሥታትም በእርሱ በመደነቅ የሚናገሩትን ያጣሉ።” #ሮም 15፥21።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in