ትንቢተ ኢሳይያስ 1
1
1ዖዝያን፥ ኢዮአታም፥ አካዝና ሕዝቅያስ የይሁዳ ነገሥታት ሆነው በነገሡባቸው ዘመናት የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፦ #2ነገ. 15፥1-7፤ 15፥32፤ 16፥20፤ 18፥1—20፥21፤ 2ዜ.መ. 26፥1—32፥33።
እግዚአብሔር ሕዝቡን መገሠጹ
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰማያት ሆይ! ስሙ፤ ምድርም አድምጪ፤ ተንከባክቤ ያሳደግኋቸው ልጆች ዐመፀኞች ሆኑብኝ፤ 3በሬ ባለቤቱን ያውቃል፤ አህያም የጌታውን ጋጥ ያውቃል፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ምንም አያውቅም፤ ሕዝቤም አያስተውልም።”
4እናንተ ኃጢአተኞች በደልን የተሸከማችሁ ወገኖች! የክፉ አድራጊዎችም ትውልድ! ሕይወታችሁ የተበላሸ፥ እግዚአብሔርን የተዋችሁና የእስራኤልን ቅዱስ የናቃችሁ በእርሱም ላይ ጀርባችሁን ያዞራችሁ ናችሁ። 5በዐመፅ ላይ ዐመፅ ጨምራችሁ እንደገና መቀጣት የምትፈልጉት ለምንድን ነው? ራሳችሁ ለሕመም፥ ልባችሁም ሁሉ ለድካም የተጋለጠ ሆኖአል። 6ከዚህም የተነሣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጒር ድረስ ጤናማ የሆነ የአካል ክፍል የላችሁም፤ ቊስልና እባጭ መግልም የሞላበት ሆኖአል፤ ይህም ቊስላችሁ አልፈረጠም፤ አልታሰረም፤ ወይም በዘይት አለሰለሰም።
7እነሆ አገራችሁ ምድረ በዳ ሆናለች፤ ከተሞቻችሁም በእሳት ጋይተዋል፤ የእርሻችሁም ቦታ ዐይናችሁ እያየ የውጪ ጠላት ይወስደዋል፤ ሁሉንም ነገር አጥፍቶ ምድራችሁን ውድማ ያደርጋታል። 8የጽዮን ልጅ በወይን አትክልት ቦታ ውስጥ እንዳለ ዳስ በዱባ ተክል ውስጥ እንዳለ ጎጆና እንደ ተከበበች ከተማ ሆናለች 9የሠራዊት አምላክ ከጥፋት የሚተርፍ ዘር ባያስቀርልንማ ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር። #ዘፍ. 19፥24፤ ሮም 9፥29።
10እናንተ የሰዶም ገዢዎች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ! የአምላካችንን ትምህርት አድምጡ፤ #አሞጽ 5፥21-22። 11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይረባኛል? እስከ አሁን ያቀረባችሁልኝ የአውራ በግ፥ የተቃጠለ መሥዋዕትና የፍሪዳ ስብ በቅቶኛል፤ በኰርማና በበግ ጠቦት፥ በአውራ ፍየልም ደም አልደሰትም። 12እኔን ለመገናኘት እንድትመጡና የመቅደሴን አደባባይ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? 13ይህን ዐይነት ከንቱ መባ ከእንግዲህ ወዲህ አታቅርቡ፤ የምታጥኑት ዕጣን በፊቴ አጸያፊ ነው፤ አዲስ ጨረቃ የምትወጣበት የወር መባቻችሁና ሰንበቶቻችሁ፥ መንፈሳዊ ስብሰባዎቻችሁም በኃጢአት የተበከሉ ስለ ሆኑ አልወደድሁላችሁም። 14አዲስ ጨረቃ የምትወጣበትን የወር መባቻችሁንና በዓሎቻችሁን ጠልቻለሁ፤ እነርሱ እንደ ከባድ ሸክም ስለ ሆኑብኝ ልታገሣቸው አልችልም።
15“እጆቻችሁን ወደ እኔ ለጸሎት ብትዘረጉ፥ ወደ እናንተ አልመለከትም፤ እጆቻችሁ በደም የተበከሉ ስለ ሆኑ የቱንም ያኽል ልመና ብታበዙ አልሰማችሁም፤ 16ይልቁንስ ታጥባችሁ ንጹሕ ሁኑ፤ ክፉ ሥራችሁን ሁሉ ከፊቴ አስወግዱ፤ በደል መፈጸማችሁንም ተዉ። 17መልካም ማድረግንም ተማሩ፤ ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ የተጨቈኑትን ታደጉ፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት ጠብቁ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ ስሙ።”
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስቲ ኑና እንወያይ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢቀላ እኔ አጥቤ እንደ በረዶ ይጸዳል፤ እንደ ደም የቀላ ቢሆን እንደ ባዘቶ ይነጣል። 19እሺ ብላችሁ ብትታዘዙኝ ምድር የምታስገኘውን በረከት ትበላላችሁ፤ 20እምቢ ብትሉኝና ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ።”
ኃጢአት የሞላባት ከተማ
21ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት እንደ አመንዝራ ሆነች! ቀድሞ ፍትሕ የሰፈነባትና የጻድቃን መኖሪያ ነበረች፤ አሁን ግን በነፍስ ገዳዮች የተሞላች ሆናለች። 22ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። 23መሪዎችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ግብረ አበሮች ሆኑ፤ እያንዳንዱ ሁልጊዜ ገጸ በረከትና ጉቦ ይቀበላል፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት አይጠብቁም፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ አይሰሙም።
24ስለዚህ፥ የእስራኤል ኀይል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በጠላቶቼ ላይ ኀይለኛ ቊጣዬን አውርጄ ተቃዋሚዎቼን እበቀላለሁ። 25በከባድ ቊጣዬ እቀጣሻለሁ፤ ከዝገትሽ አጠራሻለሁ፤ ርኲሰትሽንም በማስወገድ አነጻሻለሁ። 26ቀድሞ የነበሩሽን ዐይነት ገዢዎችንና አማካሪዎችን አስነሣልሻለሁ፤ ከዚህ በኋላ ‘እውነት የሚገኝባት ታማኝ ከተማ’ ተብለሽ ትጠሪአለሽ።”
27እግዚአብሔር እውነተኛ ስለ ሆነ ጽዮንን በፍርድ ያድናታል፤ በውስጥዋ ከሚኖሩት መካከል ንስሓ የሚገቡትን ይታደጋል። 28ኃጢአተኞችንና ዐመፀኞችን ግን በአንድነት ሰባብሮ ይደመስሳል፤ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ሁሉ ይጠፋሉ።
29በወደዳችሁት የአድባር ዛፍ ታፍሩበታላችሁ፤ በመረጣችሁትም የአትክልት ቦታ የኀፍረት መልክ ይታይባችኋል። 30በመጨረሻም ቅጠሉ እንደ ረገፈ የወርካ ዛፍና ውሃ እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁ። 31ገለባ በእሳት ብልጭታ እንደሚጋይ “ኀይለኞች ነን” የሚሉ ሰዎች ይጠፋሉ፤ እንደ ቃጠሎ እሳት በእነርሱ ላይ የሚመጣውን ጥፋት የሚያቆም የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997