ትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ
መግቢያ
ትንቢተ ኢሳይያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መቶ ዓመት መጨረሻ አካባቢ በኢየሩሳሌም ይኖር በነበረው በታላቁ ነቢይ ስም የተጠራ ነው፤ ይህ መጽሐፍ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደብ ይችላል።
1. ከም. 1-39 ያለው ክፍል የደቡባዊው መንግሥት፥ ይሁዳ፥ አሦር በተባለ ኀያል የጐረቤት መንግሥት ጥቃት ስለሚደርስበት ጊዜ የሚናገር ነው። ኢሳይያስ ይሁዳን በአደጋ ላይ የጣለው የአሦር ኀይል ሳይሆን የሕዝቡ ኃጢአትና ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ፥ እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ማጓደል እንደ ሆነ ተመለከተ፤ ግልጥ በሆነ አነጋገርና ድርጊት ነቢዩ ሕዝቡንና መሪዎቹን ጽድቅና ፍትሕ ወደሞላበት ሕይወት እንዲመለሱ በማሳሰብ፥ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ክስረትንና ጥፋትን እንደሚያስከትል አስጠነቀቃቸው። በተጨማሪ ኢሳይያስ በሚመጡት ዘመናት በዓለም ዙሪያ ሰላም የሚሰፍንበትና በፍጹምነት የሚያስተዳድር ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ የሚመጣበት ጊዜ እንዳለ አስቀድሞ ተናግሮአል።
2. ከም. 40-55 ያለው ክፍል አብዛኛው የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን ተሰዶ ውድቀትና ተስፋ መቊረጥ ስለ ደረሰበት ጊዜ የሚናገር ነው፤ ነቢዩ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ነጻ የሚያወጣበትና በአዲስ ሁኔታ ኑሮ ይመሠርቱ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመልስበት ጊዜ መቃረቡን ተናገረ፤ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ጐልቶ የሚታየው ርእስ እግዚአብሔር የታሪክ ባለቤት መሆኑንና ለሕዝቡም ያለው ዕቅድ፥ በእስራኤል አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ ሄደው መልእክት ማድረስ ያለባቸው መሆኑን የሚያስረዳው ክፍል ነው። “ስለ እግዚአብሔር አገልጋይ” የሚናገሩት ምንባቦች በብሉይ ኪዳን ከተላለፉት ታላላቅ መልእክቶች መካከል የሚቈጠሩ ናቸው።
3. ከም. 56-66 ያለው ክፍል አብዛኛውን የሚተርከው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ስለ ሄዱትና እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠውን የተስፋ ቃል ሁሉ ይፈጽም እንደሆን ማረጋገጫ ለማግኘት ስለሚፈልጉት ሕዝብ ነው፤ የተለየ ትኲረት እንዲደረግባቸው የተፈለጉት ጽድቅና ፍትሕ፥ ሰንበትን ማክበርና መሥዋዕትን ማቅረብ፥ እንዲሁም በጸሎት መትጋት ናቸው። ከዚህ ክፍል ታዋቂው ም. 61፥1-2 ሲሆን፥ ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ስለ ጥሪው ማስረጃ አድርጎ ያቀረባቸው ቃላት ይገኙባቸዋል።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
መግቢያ (1፥1-31)
ስለ ይሁዳና ስለ እስራኤል የተላለፉ መልእክቶች (2፥1—5፥30)
ስለ ይሁዳና እስራኤል ተጨማሪ መልእክቶች (9፥8—12፥6)
የእግዚአብሔር ቅጣት በሌሎች ሕዝቦች ላይ (13፥1—23፥18)
ለሚሠቃዩት የእግዚአብሔር ሕዝብ የተስፋ መልእክት (24፥1—27፥13)
እግዚአብሔር ዐመፀኛ ሕዝቡን የሚቀጣ መሆኑ (28፥1—31፥9)
እግዚአብሔር ኤዶምን የሚቀጣ፥ ኢየሩሳሌምን ግን የሚባርክ መሆኑ (32፥1—35፥10)
አሦር፥ ባቢሎን፥ ንጉሥ ሕዝቅያስና ኢሳይያስ (36፥1—39፥8)
እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድን መሆኑ (40፥1—48፥22)
የእግዚአብሔር አገልጋይ (49፥1—53፥12)
እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚጠብቅ (54፥1—55፥13)
ሕዝቦች ሁሉ የእግዚአብሔር ወገኖች ለመሆን እንደሚችሉ (56፥1-8)
ለእግዚአብሔር ታማኞች ያልሆኑ መሪዎች እንደሚቀጡ (56፥9—59፥21)
የኢየሩሳሌም የወደፊት የክብር ተስፋ (60፥1—62፥12)
የእግዚአብሔር አዲሱ ድንቅ ፍጥረት (63፥1—66፥24)
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997