YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መክብብ 5

5
እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚደረግ አክብሮት
1ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትገባበት ጊዜ ለአረማመድህ ጥንቃቄ አድርግ፤ እዚያ ሄዶ ደጉን ከክፉ ለይተው የማያውቁ ሞኞች ሰዎች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ የምክር ቃላትን ለመስማት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይበልጣል። 2ከመናገርህ በፊት አስብ፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በችኰላ ስእለት አታድርግ፤ እግዚአብሔር በሰማይ አንተ ግን በምድር መሆንህን በማሰብ የምትናገረው ቃል የተመጠነ ይሁን። 3ስለ አንድ ነገር ብታስብ ስለ እርሱ ታልማለህ፤ ብዙ ከመናገር የተነሣ ትሳሳታለህ፤ 4ስለዚህ እግዚአብሔር በሞኞች አይደሰትም፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በተሳልክ ጊዜ ወዲያውኑ የተሳልከውን ለመፈጸም ዝግጁ ሁን፤ #መዝ. 66፥13-14። 5ተስለህ የማትፈጽመው ከሆነ ግን ቀድሞውንም ባትሳል የተሻለ ነው። 6ወደ ኃጢአት እንዳይመራህ ለአንደበትህ ከገደብ ያለፈ ነጻነት አትስጠው፤ በዚህ ዐይነት “ይህን የተናገርኩት ሳላውቅ ነው” ብለህ በእግዚአብሔር አገልጋይ ፊት ይቅርታ ከመጠየቅ ትድናለህ፤ አለበለዚያ ግን የደከምክበትን ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቊጣ በገዛ እጅህ እንደ መጋበዝ ይሆንብሃል። 7ብዙ ሕልምና ብዙ ልፍለፋ ከንቱ ነው፤ ከዚህስ ይልቅ እግዚአብሔርን ፍራ።
የኑሮ ከንቱነት
8በአንድ አገር ግፍ ሲሠራና መብት በመንፈግ ፍትሕ ሲጓደል ባየህ ጊዜ አትደነቅ፤ እያንዳንዱ ገዥ የበላይ ተመልካች አለው፤ ከሁሉም በላይ የሆነ ሌላ ተመልካች ደግሞ አለ። 9የመሬት ምርት መጨመር ሁሉንም ይጠቅማል፤ ንጉሡ ራሱ ከእርሻው ይጠቀማል።
10ብርን የሚወድ ብር አግኝቶ አይጠግብም፤ ሀብታም ለመሆን የሚፈልግም ሰው ትርፍ አግኝቶ በቃኝ አይልም፤ ይህም ከንቱ ነው። 11ሀብት ሲበዛ በዚያው መጠን በላተኛው ይበዛል፤ ታዲያ፥ አይቶ ከመደሰት በቀር ለባለቤቱ ምን የሚተርፈው ነገር አለ? 12የጉልበት ሥራ የሚሠራ ሰው ብዙም ሆነ ጥቂት ቢመገብ የሰላም እንቅልፍ አግኝቶ ያድራል፤ የባለ ጸጋ ሰው የሀብት ብዛት ግን ሀብቱ እንቅልፍ ይነሣዋል።
13-14በዚህ ዓለም እጅግ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ደግሞ አየሁ፤ ይኸውም ሰዎች ለክፉ ቀን ይጠቅመናል ብለው ሀብት ያከማቻሉ፤ ነገር ግን በአንድ መጥፎ አጋጣሚ ሀብታቸውን ያጡና ለልጆቻቸው የሚተላለፍ ምንም ነገር ሳይተርፋቸው ይቀራል። 15ሰው ሁሉ ራቁቱን እንደ ተወለደ ባዶ እጁን ተመልሶ ይሄዳል፤ የቱንም ያኽል በሥራ ቢደክም ይዞት የሚሄደው ነገር የለም። #ኢዮብ 1፥21፤ መዝ. 49፥17፤ 1ጢሞ. 6፥7። 16ራቁቱን እንደ ተወለደ ራቁቱን መሄዱ እጅግ የሚያሳዝን ነው፤ ድካሙ ሁሉ ነፋስን እንደ መጨበጥ ከንቱ ከሆነ ጥቅሙ ምንድን ነው? 17ዕድሜውንም የሚፈጽመው ጨለማ በወረሰው ሕይወት፥ በሐዘን፥ በሚያስጨንቅ ሐሳብ፥ በብስጭትና በሕመም ነው።
18እንግዲህ እኔ የተመለከትኩት የተሻለ ነገር ቢኖር ሰው በዚህ ዓለም ሳለ እግዚአብሔር በሰጠው አጭር ዕድሜ የደከመበትን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት መደሰቱ ነው፤ የሰው ዕድል ፈንታም ይኸው ብቻ ነው። 19እግዚአብሔር ለሰው ሀብትና ብልጽግናን መስጠቱ የደከመበትን ድርሻ አግኝቶ በመብላትና በመጠጣት ደስ እንዲለው ፈቅዶለት ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20እግዚአብሔርም በዚህ ሁሉ የልብ ደስታን ስለ ሰጠው በዕድሜው ማጠርና መርዘም ከመጠን በላይ አይጨነቅም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in