YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መክብብ 4

4
ጭቈና፥ ድካምና ወዳጅ አልባ መሆን
1እንደገናም በዓለም ያለውን የፍርድ መጓደልና ግፍ ተመለከትኩ፤ የተገፉ ጭቊኖች የሚያጽናናቸው አጥተው ያለቅሱ ነበር፤ የፈላጭ ቈራጭነት ሥልጣን በገዢዎቻቸው እጅ ስለ ሆነ የሚረዳቸው አላገኙም። 2ስለዚህም እኔ “በዚህ ሁኔታ ላይ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱት ይሻላሉ” አልኩ። 3በተለይም ከነዚህ ከሁለቱ ወገኖች ይልቅ ከቶውኑ ያልተወለዱና በዚህ ዓለም የሚፈጸመውን ግፍና ጭቈና ያላዩ ዕድለኞች ናቸው።
4ደግሞም ሰዎች የተመኙትን ለማግኘት ተግተው በመሥራት ምን ያኽል እንደሚደክሙ ተመለከትኩ፤ ይህንንም የሚያደርጉት በባልንጀሮቻቸው ላይ በመቅናት መሆኑን ተረዳሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው። 5እጆቹን አጥፎ የሚቀመጥ ሞኝ ሰው ራሱን በራብ ይገድላል። 6ነፋስን እንደ መጨበጥ ከሚቈጠር ላልተጨበጠ ሐሳብ ብዙ አገኛለሁ ብሎ ከመድከም ይልቅ ከኅሊና ዕረፍት ጋር ጥቂት ለማግኘት መሥራት ይሻላል።
7በዚህ ዓለም ያለውን ሌላውንም ከንቱ ነገር ተመለከትኩ፤ 8እነሆ፥ ብቻውን የሚኖር አንድ ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁን እንጂ ዘወትር በሥራ ከመድከም አይቦዝንም፤ ባገኘውም ሀብት በቃኝ ማለትን አላወቀም፤ “እርሱም የምደክመው ለማን ነው? ለራሴስ ደስታን የምነፍገው ለምንድን ነው?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል፤ ይህ ሁሉ የባሰ ከንቱና የሥቃይ ሕይወት ነው።
9የሥራቸው ውጤት መልካም ሊሆን ስለሚችል አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። 10ከሁለቱ አንዱ ቢወድቅ ሌላው ያነሣዋል፤ ብቻውን የሆነ ሰው ቢወድቅ እንኳ የሚያነሣው ረዳት ስለሌለው ወዮለት። 11ሁለቱ አብረው ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ ብቻውን የሚተኛ ሰው ግን እንዴት ሊሞቀው ይችላል? 12አንድ ሰው ብቻውን ሊመልሰው የማይችለውን አደጋ ሁለት ሰዎች ሊቋቋሙት ይችላሉ፤ በሦስት ተሸርቦ የተገመደ ፈትል እንኳ በቀላሉ አይበጠስም።
13ምክርን ከማይቀበል ከሞኝ ሽማግሌ ንጉሥ ብልኅ ድኻ ወጣት ይሻላል። 14ምንም እንኳ አንድ ሰው ከድኻ ቢወለድና እስረኛ የነበረ ቢሆንም ንጉሥ ለመሆን ይችላል። 15አንድ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ሁሉ በንጉሡ ቦታ የሚተካውን ወጣት ሲከተሉ አየሁ። 16ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድርበት ጊዜ የሚገዛለት ሕዝብ ብዛት እጅግ ብዙ ነው፤ ከዙፋኑ ላይ በታጣ ጊዜ ግን ስላደረገው ነገር ሁሉ የሚያመሰግነው አንድ ሰው እንኳ አይገኝለትም፤ ይህም ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር የሚቈጠር ከንቱ ነገር ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in