YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ አሞጽ 8

8
አሞጽ የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት በራእይ ማየቱ
1ጌታ እግዚአብሔር ሌላ ራእይ ገለጠልኝ፤ እነሆ የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት አየሁ፤ 2እግዚአብሔርም “ይህ የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ።
እኔም “የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት አያለሁ” አልኩት።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ “የሕዝቤ የእስራኤል ፍጻሜ ደርሶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነርሱን ከመቅጣት አልመለስም። 3በቤተ መንግሥት የሚያሰሙት ዘፈን በዚያን ቀን ወደ ለቅሶ ይለወጣል፤ የብዙ ሰው ሬሳ በየቦታው ወድቆ ይገኛል፤ በዝምታም በየስፍራው ይጣላል።”
የእስራኤል ውድቀት
4እናንተ የችግረኞችን መብት የምትረግጡና ድኾችን ከአገር ለማጥፋት የምትፈልጉ ሁሉ! ይህን ስሙ! 5እናንተ እንዲህ ትላላችሁ፦ “እህላችንን መሸጥ እንድንችል የወር መባቻው በዓል ምነው ቶሎ ባለፈልን! ስንዴ ወደ ገበያ ለመውሰድ ሰንበትም መቼ ያልፍልናል? በዓላቱ ካለፉልን የእህሉን መስፈሪያ አሳንሰን ከፍተኛ ዋጋ እንጠይቃለን፤ በሐሰተኛ ሚዛንም ሕዝቡን እናታልላለን፤ 6የስንዴውን ግርድ እንኳ እንሸጣለን፤ ድኻውን በብር ችግረኛውንም በአንድ ጥንድ ነጠላ ጫማ እንገዛለን።”
7ለያዕቆብና ለዘሮቹ መመኪያ የሆነው እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ማለ፦ “እነርሱ የሠሩትን ሥራ ሁሉ አልረሳም። 8በዚህ ነገር ምድር ትናወጣለች፤ በአገሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የዓባይ ወንዝ ሞልቶ በመጒደል እንደሚናወጥ አገሪቱ በሞላ ትናወጣለች።” 9ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ገና በእኩለ ቀን ፀሐይ እንድትጠልቅ አደርጋለሁ፤ በቀትርም ምድሪቱን አጨልማለሁ። 10የዓመት በዓል ደስታችሁን ወደ ሐዘን፥ ዘፈናችሁንም ወደ ለቅሶ እለውጠዋለሁ፤ አንድ ብቻ የሆነ ልጃቸው ሞቶባቸው እንደሚያለቅሱ ወላጆች ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ ማቅ እንድትለብሱ አደርጋለሁ፤ የዚያ ቀን ፍጻሜ የመረረ ይሆናል።
11“እነሆ በምድር ላይ ራብን የማመጣበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም ሰዎች የሚራቡትና የሚጠሙት የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ነው እንጂ ምግብና ውሃ በማጣት አይደለም፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 12ሕዝቡ ሁሉ ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የእግዚአብሔርንም ቃል ለማግኘት በሁሉ ቦታ ይንከራተታሉ፤ ነገር ግን አያገኙም። 13በዚያን ጊዜ ቆነጃጅት ልጃገረዶችና ጠንካራ ወንዶች ወጣቶች እንኳ ከመጠማት የተነሣ ይዝላሉ፤ 14‘አሺማ’ ተብላ በምትጠራ በሰማርያ ሴት አምላክ የሚምሉ ‘በዳን አምላክ’ ወይም ‘በቤርሳቤህ አምላክ’ እያሉ የሚምሉ ሁሉ ይወድቃሉ፤ ከወደቁበትም ፈጽሞ መነሣት አይችሉም።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in