YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ አሞጽ 9

9
የእግዚአብሔር ፍርድ
1እግዚአብሔርን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ የቤተ መቅደሱን ጒልላት ምታ፤ ሰባብረህም በሰዎቹ አናት ላይ እንዲደረመስ አድርግ፤ ከዚያ የተረፉትንም እኔ በሰይፍ እጨርሳቸዋለሁ፤ ማንም መሸሽ አይችልም፤ ማንም ሊያመልጥ አይችልም። 2ምድርን ቆፍረው ወደ ሙታን ዓለም ቢወርዱ እንኳ እኔ ከዚያ መንጥቄ አወጣቸዋለሁ፤ ወደ ሰማይም መጥቀው ቢወጡ እንኳ እኔ መልሼ አወርዳቸዋለሁ፤ 3በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ወጥተው ቢሸሸጉም ተከታትዬ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ ወደ ጥልቅ ባሕር ገብተው ከእኔ ለመሰወር ቢሞክሩም እንዲነድፋቸው የባሕሩን ዘንዶ አዛለሁ። 4በጠላቶቻቸው እጅ ተማርከው ቢወሰዱም እዚያ እንዲገደሉ አደርጋለሁ፤ በዚህ ዐይነት እኔ በእነርሱ ላይ የማደርገው ትኲረት ይጐዳቸዋል እንጂ አይጠቅማቸውም።”
5መላዋ ምድር እንደ ግብጹ የዐባይ ወንዝ
ከፍና ዝቅ በማለት ትናወጣለች፤
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሲነካ ትቀልጣለች፤
በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ።
6መኖሪያውን በሰማያት ያደረገ፥
ጠፈርን ከምድር በላይ ያጸና፥
የባሕሩን ውሃ አዞ
በምድር ላይ እንዲፈስ የሚያደርግ፥
ስሙ እግዚአብሔር ነው።
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእኔ ዘንድ ኢትዮጵያውያን ከእናንተ አያንሱም፤ እናንተን ከግብጽ እንዳወጣሁ እንደዚሁም ፍልስጥኤማውያንን ከቀርጤስ፥ ሶርያውያንን ከቂር አላወጣሁምን? አውጥቻለሁ። 8እኔ ጌታ እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኛው የእስራኤል መንግሥት እመለከታለሁ፤ እርስዋንም ከምድር ገጽ አጠፋለሁ፤ ሆኖም የያዕቆብን ዘር ሙሉ በሙሉ አልደመስስም። ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9“የእስራኤል ሕዝብ በሕዝቦች መካከል እንዲበተኑ አዛለሁ፤ የሚበተኑትም እህል በወንፊት እንደሚነፋ ዐይነት ነው፤ ነገር ግን ወንፊቱ ሲነቃነቅ ገለባው እንጂ አንድም ቅንጣት አይበተንም። 10‘ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም ወይም አያገኘንም’ የሚሉ በሕዝቤ መካከል የሚገኙ ኃጢአተኞች ሁሉ በጦርነት ይሞታሉ።”
የእስራኤል ሕዝብ የመመለስ ተስፋ
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ፈራርሶ እንደ ወደቀ ቤት የነበረውን የዳዊትን ሥርወ መንግሥት መልሼ የማቋቊምበት ጊዜ ይመጣል፤ ቅጽሩን እጠግናለሁ፤ ፍርስራሹንም አድሳለሁ፤ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበረውም አድርጌ እሠራዋለሁ፤ 12በዚህም ዐይነት ከኤዶም ምድር የተረፉትንና ሌሎችንም በስሜ የተጠሩትን ሕዝብ ሁሉ ይወርሳሉ፤” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። #ሐ.ሥ. 15፥16-18።
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የእህል ሰብል አጫጆች አጭደው ሳይጨርሱ፥
አራሾች የሚደርሱባቸውና ወይን ጨማቂዎችም
የወይን ፍሬ ጨምቀው ሳይጨርሱ፥
የወይን ተካዮች የሚደርሱባቸው ጊዜ ይመጣል፤
በዚያን ጊዜ ተራራዎች ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያፈልቃሉ፤
ኰረብቶችም በወይን ጠጅ ይጥለቀለቃሉ።
14ሕዝቤን እስራኤልን ወደ አገራቸው መልሼ አመጣለሁ፤
የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ሠርተው በዚያ ይኖራሉ፤
ወይን ተክለው የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤
ልዩ ልዩ ተክሎችን ተክለው ፍሬውን ይመገባሉ።
15ሕዝቤን እስራኤልን በሰጠኋቸው ምድር ላይ እተክላቸዋለሁ፤
ዳግመኛም ከዚያ ተነቅለው አይወጡም፤”
ይህን የሚናገር እግዚአብሔር አምላካችሁ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in