YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሚክያስ መግቢያ

መግቢያ
ሚክያስ በኢሳይያስ ጊዜ የነበረ ነቢይ ሲሆን፥ ተወላጅነቱም በደቡባዊው የይሁዳ ንጉሣዊ መንግሥት ውስጥ በምትገኝ በአንዲት የገጠር ከተማ ነበር። ልክ አሞጽ በሰሜናዊው ንጉሣዊ መንግሥት ላይ ጥፋት እንደሚደርስ እንደ ተናገረው ሁሉ ሚክያስም በነዚያው ምክንያቶች በይሁዳም ንጉሣዊ መንግሥት ላይ ጥፋት እንደሚደርስ ተነበየ፤ ሕዝቡ በሚፈጽሙት አጸያፊ የሆነ የፍትሕ መጓደል ላይ እግዚአብሔር ፍርድን እንደሚያመጣ አስጠነቀቀ፤ ይሁን እንጂ የሚክያስ የትንቢት ቃል ወደ ፊት ተስፋ መኖሩን የሚያመለክት ብዙ ምልክቶችንም ጨምሮ ያቀፈ ነው።
በተለይ ትኲረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ክፍሎች በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ዓለም ዐቀፋዊ ሰላም እንደሚኖር (ከም. 4፥1-4)፥ ከዳዊት ሥርወ መንግሥት ታላቅ ንጉሥ እንደሚወጣና ለሕዝቡ ሰላምን እንደሚሰጥ (ከም. 5፥2-4)፥ እንዲሁም የእስራኤል ነቢያት የተናገሩት ቃል ሁሉ በአንዲት ጥቅስ እንደ ተጠቃለለ የሚገልጡት ናቸው፤ ያቺም ጥቅስ የምትለው እንዲህ ነው፦
“እርሱ ከእኛ የሚፈልገው ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግ፥ ደግነት የተሞላበትን ፍቅር እንድናሳይና ከአምላካችን ጋር በፍጹም ትሕትና እንድንራመድ ነው።” (6፥8)
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
1. ጌታ ሕዝቡን ይቀጣል (1፥1—2፥11)
2. የወደፊት ተስፋ (2፥2-13)
3. እግዚአብሔር ክፉ መሪዎችንና ሐሰተኞች ነቢያትን ይቀጣል (3፥1- 12)
4. በአዲሲትዋ እስራኤል አዲስ ቤተ መቅደስ (4፥1—5፥15)
5. የእስራኤል በደለኛነት መገለጡ (6፥1—7፥7)
6. የሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር መመለስ (7፥8-20)

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in