YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ አሞጽ 5

5
የእስራኤል ሕዝብ ወደ ንስሓ መጠራት
1የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእናንተ ላይ እኔ የማወርደውን ይህን ሙሾ አድምጡ፦
2እነሆ ድንግሊቱ እስራኤል ወደቀች፤
እንደገናም መነሣት አትችልም
የሚያነሣት ረዳት በማጣት
በገዛ ምድርዋ የተተወች ብቸኛ ሆነች።
3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከአንዲት የእስራኤል ከተማ ሺህ ጦረኞች ይዘምታሉ፤ በሕይወት የሚቀሩት ግን አንድ መቶ ብቻ ይሆናሉ፤ ከሌላይቱም ከተማ መቶ ጦረኞች ይዘምታሉ፤ ተመልሰው የሚመጡት ግን ዐሥር ብቻ ይሆናሉ።”
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ እኔ ተመለሱ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ 5ወደ ቤርሳቤህ አትሂዱ፤ ቤቴል ፈራርሳ እንዳልነበረች ስለምትሆን በጌልገላ የሚኖሩ ሕዝቦችም ስደት ስለ ተፈረደባቸው ወደ ቤቴልም ሆነ ወደ ጌልጌላ አትሂዱ።”
6ይልቅስ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ አለበለዚያ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንደ እሳት ሆኖ ያጋያቸዋል፤ የቤትኤልንም ኗሪዎች እሳት ይበላቸዋል፤ እሳቱን የሚያጠፋላቸውም አይገኝም። 7እናንተ ፍርድን የምታጣምሙና እውነትን ወደ ሐሰት የምትለውጡ ወዮላችሁ!
8-9“ፕሊያዲስ” የተባሉትን ሰባቱን ከዋክብትና
“ኦርዮን” ተብለው የሚጠሩትን
የከዋክብት ክምችትን የፈጠረ፥
ሌሊቱን ወደ ቀን፥ ቀኑንም ወደ ሌሊት የሚለውጥ፥
የባሕሩን ውሃ አዞ፥
በምድር ላይ እንዲፈስ የሚያደርግ፥
ኀያላንንና ምሽጎቻቸውን የሚደመስስ እርሱ ነው፤
ስሙም እግዚአብሔር ነው። #ኢዮብ 9፥9፤ 38፥31።
10እናንተ በፍርድ አደባባይ የሚገሥጻችሁን ጠላችሁ፤ እውነት የሚናገረውንም ተጸየፋችሁ። 11ድኾችን ጨቊናችሁ፤ እህላቸውንም አስገብራችሁ፤ ከጥርብ ድንጋይ ቤቶች ሠርታችኋል፤ እናንተ ግን አትኖሩባቸውም፤ የሚያስደስት ወይን ተክላችኋል፤ ነገር ግን ከእርሱ የሚገኘውን የወይን ጠጅ እናንተ አትጠጡም። 12በደላችሁ ምን ያኽል እንደ በዛና ኃጢአታችሁም ምን ያኽል ከባድ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ደጋግ ሰዎችን ታስጨንቃላችሁ፤ ጉቦ እየተቀበላችሁ በየፍርድ አደባባዩ የምስኪኖችን ፍትሕ ታጣምማላችሁ። 13ስለዚህ ዘመኑ ክፉ ስለ ሆነ አስተዋይ የሆነ ሰው ዝም ይላል።
14በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉ ነገር አታድርጉ፤ ይህን ብታደርጉ ልክ እናንተ እንደምትሉት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል። 15ክፉውን ነገር ጥሉ፤ መልካም የሆነውን ነገር ውደዱ፤ በየፍርድ አደባባዩም ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለተረፉት የእስራኤል ሕዝብ ምሕረት ያደርግላቸው ይሆናል።
16ስለዚህ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በየመንገዱና በየአደባባዩ ዋይታና ለቅሶ ይሰማል፤ ገበሬዎች እንኳ ለለቅሶ ይጠራሉ፤ ከሙሾ አውጪዎችም ጋር ስለ ሞቱ ሰዎች ያለቅሳሉ፤ 17በወይን ተክል ቦታዎች ሁሉ ለቅሶ ይሆናል፤ ይህም ሁሉ የሚሆነው እኔ በመካከላችሁ ስለማልፍ ነው፤” ይህንንም የተናገረ እግዚአብሔር ነው።
18እናንተ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ ወዮላችሁ! ያ ቀን የጨለማ እንጂ የብርሃን ቀን ስላይደለ ለምን ያንን ቀን ትጠባበቃላችሁ? 19ያ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሸሽቶ ሲሄድ ድብ እንደሚያጋጥመው፥ ወይም አምልጦ ወደ ቤቱ ሲገባ እጁን በግድግዳ ላይ ቢያሳርፍ እባብ እንደሚነድፈው ሁኔታ ይሆንባችኋል። 20በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ጨለማ እንጂ ብርሃን አይሆንላችሁም፤ ያ ቀን ምንም ብርሃን የማይታይበት ድቅድቅ ጨለማ ይሆንባችኋል።
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዓመት በዓሎቻችሁን ሁሉ እጠላለሁ፤ እንቃለሁም፤ የአምልኮ ስብሰባዎቻችሁም አያስደስቱኝም። 22የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ ብታቀርቡልኝ እንኳ አልቀበላችሁም፤ ለደኅንነት መሥዋዕት ወደምታቀርቡልኝ የሰቡ ፍሪዳዎችም አልመለከትም። #ኢሳ. 1፥11-14። 23የመዝሙራችሁን ጩኸት ከእኔ አርቁ፤ የበገናችሁንም ዜማ መስማት አልፈልግም፤ 24ይልቅስ ፍትሕ እንደ ወራጅ ውሃ፥ ጽድቅም እንደማያቋርጥ የወንዝ ውሃ ይፍሰስ።
25“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በውኑ በአርባው ዓመት የምድረ በዳው ጒዞ ጊዜ መሥዋዕትና መባ አቅርባችሁልኛልን? #ሐ.ሥ. 7፥42-43። 26ለራሳችሁ የሠራችኋቸውን ‘ንጉሥ የምትሉትን’ ሳኩት የተባለውን ጣዖታችሁን፥ እንዲሁም ‘ኬዋን’ የተባለውን የኮከብ ጣዖታችሁን ትሸከማላችሁ። 27ከደማስቆ ወዲያ ርቃችሁ እንድትሰደዱ አደርጋለሁ።” ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነኝ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in