YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ አሞጽ 4

4
1እንደ ባሳን ቅልብ ላሞች ሰውነታችሁን ያወፈራችሁ የሰማርያ ሴቶች ሆይ! ይህን ቃል አድምጡ! እናንተ ደካሞችን ታዋርዳላችሁ፤ ድኾችን ትጨቊናላችሁ፤ ባሎቻችሁ ሁልጊዜ የሚያሰክር መጠጥ እንዲያቀርቡላችሁ ትጠይቃላችሁ። 2ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር በቅድስናው እንዲህ ሲል ምሎአል፦ “እናንተ በመንጠቆ ተይዞ እንደሚወሰድ ነገር የምትወሰዱበት ጊዜ ይመጣል፤ ከእናንተ እስከ መጨረሻ የቈዩት እንኳ በመንጠቆ ተይዘው እንደሚወሰዱ ዐሣዎች ይወሰዳሉ። 3እያንዳንዳችሁ በአቅራቢያችሁ በሚገኘው መሹለኪያ ቀዳዳ ተጐትታችሁ በመውጣት ወደ ሃርሞን ትጣላላችሁ።”
የእስራኤል ሕዝብ ከስሕተት አለመማር
4ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ ቤትኤል ሄዳችሁ ኃጢአት ሥሩ! ወደ ጌልጌላም ሂዱና የበለጠ በደል ፈጽሙ! በየዕለቱ መሥዋዕታችሁን አቅርቡ! በየሦስተኛውም ቀን ዐሥራታችሁን ስጡ። 5እናንተም ማድረግ የምትፈልጉት ይህንኑ ስለ ሆነ፥ የምስጋና ቊርባን የሆነውን የኅብስት መባችሁን አቅርቡ፤ በፈቃዳችሁም ስለምታቀርቡት መሥዋዕት ዐዋጅ ንገሩ።”
6“በአፋችሁ የምትቀምሱት እህል አሳጥቼ በከተሞቻችሁ ሁሉ ችጋር ለቅቄባችኋለሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። 7አዝመራችሁ ከመድረሱ ከሦስት ወር በፊት ዝናብ እንዲቋረጥ አደረግሁ፤ በአንድ ከተማ ሲዘንብ በሌላው ከተማ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ ለአንዱ እርሻ ሲዘንብለት ሌላው እርሻ ዝናብ አጥቶ ደረቀ። 8ሰዎች ውሃ መጠጣት ፈልገው ከከተማ ወደ ከተማ ሄዱ፤ ነገር ግን በቂ ውሃ ባለማግኘታቸው ጠጥተው ሊረኩ አልቻሉም፤ እናንተም ወደ እኔ አልተመለሳችሁም።
9“ሰብላችሁን የሚያደርቅ ብርቱ ነፋስ ላክሁባችሁ፤ አትክልታችሁንና የወይን ተክላችሁን የበለስና የወይራ ዛፋችሁን ሁሉ አንበጣ በላው፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም።
10“በግብጽ ምድር የላክሁትን ዐይነት መቅሠፍት ላክሁባችሁ፤ ጐልማሶቻችሁ በሰይፍ እንዲሞቱ፥ ፈረሶቻችሁም እንዲማረኩ አደረግሁ፤ በሰፈራችሁ በሞቱ ሰዎች የበድን ግማት አፍንጫችሁን ሞላሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም።
11“ሰዶምንና ገሞራን እንደ ደመሰስኩ ከእናንተም ብዙዎችን ደመሰስኩ፤ እናንተም የተረፋችሁት በእሳት ከተቀጣጠለ በኋላ ተነጥቆ እንደ ወጣ እንጨት ነው፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። #ዘፍ. 19፥24። 12የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነሆ እኔም እንደዚሁ አደርግባችኋለሁ፤ ስለዚህ ይህን ስለማደርግባችሁ ከእኔ ከአምላካችሁ ጋር በፍርድ ለመገናኘት ተዘጋጁ!”
13ተራራዎችን የሠራ፥
ነፋሶችን የፈጠረ፥
ያሰበውን ነገር ለሰው የሚገልጥ፥
የቀኑን ብርሃን ወደ ጨለማ የሚለውጥ፥
በምድር ከፍታዎች ላይ የሚራመድ፥
ስሙ የሠራዊት አምላክ
እግዚአብሔር ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in