ትንቢተ አሞጽ 3
3
በእስራኤል ላይ የተነገረ ትንቢት
1የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከግብጽ ባወጣችሁ፥ በእናንተ በመላው ሕዝብ ላይ እግዚአብሔር የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ 2“በዓለም ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የመረጥኩት እናንተን ብቻ ነው፤ በምትሠሩት ኃጢአት ሁሉ የምቀጣችሁ ስለዚህ ነው።”
3ሁለት ሰዎች አብረው ለመሄድ ካልተቀጣጠሩ በቀር በአንድነት ለመሄድ ይችላሉን?
4አንበሳ በደን ውስጥ ዐድኖ የሚበላውን ሳያገኝ በከንቱ ያገሣልን?
የአንበሳ ደቦልስ አንዳች ነገር ዐድኖ ሳይዝ በሚኖርበት ቦታ ድምፁን ያሰማልን?
5ወፍ ያለ ማጥመጃ ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ይያዛልን?
ወጥመድስ አንዳች ነገር ሳይነካው ይፈናጠራልን?
6ለጦርነት የሚያዘጋጅ መለከት በከተማ ውስጥ ሲነፋ በፍርሃት የማይንቀጠቀጥ ሕዝብ ይኖራልን?
እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር በከተማ ላይ ክፉ ነገር ይመጣልን?
7ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት አስቀድሞ ሳይገልጥ ምንም ነገር አያደርግም።
8አንበሳ ሲያገሣ ሰምቶ የማይፈራ ማን አለ?
ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ሲገልጥለት ትንቢት የማይናገር ማን አለ?
የሰማርያ ውድቀት
9በአሽዶድና በግብጽ በሚገኙ ምሽጎች ለሚኖሩ ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፦ “በሰማርያ ተራራ ላይ ተሰብሰቡ፤ እዚያ ውስጥም የሚፈጸመውን ግፍና ያለውን ሁከት ተመልከቱ።”
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ሕዝቦች መልካም ነገር ማድረግን አያውቁም፤ በዐመፅና በግፍ በተወሰደ ንብረት ምሽጋቸውን ይሞላሉ፤ 11ስለዚህ ጠላት አገራቸውን ይከባል፤ ምሽጎቻቸውንም አፈራርሶ ቤቶቻቸውን ይዘርፋል።”
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሰማርያ የሚኖሩ እስራኤላውያን ከአልጋና ከድንክ አልጋ ቊራጭ ጋር ያመልጣሉ፤ ይኸውም እረኛ ከአንበሳ መንጋጋ ሁለት እግርና የጆሮ ቊራጭ ለማስጣል እንደሚችለው ዐይነት ነው።” 13የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ይህን ስሙ፤ በያዕቆብ ዘሮች ላይ መስክሩ። 14ስለ ሠሩት ኃጢአት የእስራኤልን ሕዝብ በምቀጣበት ቀን በቤትኤል የሚገኙትን መሠዊያዎች አፈራርሳለሁ፤ የመሠዊያዎቹም ቀንዶች ተሰባብረው በምድር ላይ ይወድቃሉ። #2ነገ. 23፥15። 15የክረምቱንና የበጋውን ወራት የሚያሳልፉባቸውን ቤቶች ሁሉ እደመስሳለሁ፤ በዝሆን ጥርስ አጊጠው የተሠሩ ቤቶች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ታላላቅ ቤቶች ሁሉ ይወድማሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997